“በጸጥታው ችግር ምክንያት ለጥቃት ተጋላጭ የኾኑ ሴቶችን ለመደገፍ እየተሠራ ነው” የምዕራብ ጎጃም ዞን

23

ፍኖተ ሰላም: ጥር 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎጃም ዞን ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ “የሴቶች የተደራጀ እና ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለዘላቂ ሰላም እና ልማት ግንባታ” በሚል መሪ መልዕክት ከሴት የመንግሥት ሠራተኞች ጋር የውይይት መድረክ በፍኖተ ሰላም ከተማ አካሂዷል።

መድረኩ ላይ የተገኙት የምዕራብ ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፓለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ሙላት ጌታቸው ክልሉ የገጠመው የሰላም እጦት በኢኮኖሚ፣ በፓለቲካ እና በማኅበራዊ ዘርፎች በርካታ ቀውሶችን እያደረሰ መኾኑን ተናግረዋል።

ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት የመጀመሪያ ተጠቂዎች ሴቶች መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ለሰላም ግንባታ የሴቶች ሚና የጎላ በመኾኑ የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባልም ነው ያሉት።

ሴቶች በማኅበራዊ፣ በፓለቲካ እና ኢኮኖሚ ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ ወሳኝ ነውም ብለዋል፡፡ ሴቶች ሰላምን ለመጠበቅ እና ለማሳደግም ዓይነተኛ አበርክቶ እንዳላቸው አስገንዝበዋል።

በጸጥታው ችግር ምክንያት ለጥቃት ተጋላጭ የኾኑ ሴቶችን በሴቶች ማኅበራት በማስተባበር የመደገፍ ሥራ እየተሠራ መኾኑን የምዕራብ ጎጃም ዞን ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ስለእናት ዘሪሁን ተናግረዋል ።

በተለይም የሴት አደረጃጀቶችን በማጠናከር ሴቶች ለሰላም ግንባታ የበኩላቸውን እንዲወጡ እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ታጥቀው ወደ ጫካ የገቡ ኀይሎችም ፊታቸውን ወደ ሰላም እንዲያዞሩ ነው መምሪያ ኀላፊዋ የጠየቁት።

ሴቶች በማኅበራዊ፣ በፓለቲካ እና ኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ሁሉ አደረጃጀቶችን በመጠቀም የሰላም ግንባታ ሂደት ላይ ተሳትፏቸውን የማጠናከር ሥራ እየተከናወነ መኾኑንም የምዕራብ ጎጃም ዞን ሴቶች ሊግ ኀላፊ አክሊለ ዞማነህ ገልጸዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የተሳተፉ ሴት የመንግሥት ሠራተኞችም የጸጥታ ችግሩ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ተረድተው እንዲሠሩ ነው ያስገነዘቡት፡፡

ከዚህ የከፋ ችግር እንዳይከሰትም ሁሉም አካላት ለውይይት ዝግጁ መኾን እንደሚገባቸው ነው የጠቆሙት፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁሉም ማኅበረሰብ ሊረባረብ ይገባል ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሕግ የበላይነት ለማረጋገጥ የኅብረተሰቡ ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡
Next articleከ290 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ እየለማ መኾኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።