
ደባርቅ: ጥር 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ጎንደር ዞን ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ የስድስት ወራት የሕግ የማስከበር ተግባራት አፈፃፀም ግምገማ እና የቀጣይ አቅጣጫ የውይይት መድረክ በደባርቅ ከተማ አካሂዷል። በአማራ ክልል ከ2015 ዓ.ም ሐምሌ ወር ጀምሮ በተቀሰቀሰ ግጭት በርካታ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመት መድረሱ ይታወሳል።
የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ በክልሉ ዝርፊያ፣ እገታ፣ ግድያ እና ሌሎች መሰል የወንጀል ተግባራቶች ተበራክተው መቆየታቸው ተደጋግሞ ሲገለጽ ቆይቷል። የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ በሪሁን መንግሥቱ በክልሉ የተከሰተውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት እና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን መንግሥት ቅድሚያ ለሰላም ሰጥቶ ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ በማድረግ ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት አሳይቷል ብለዋል።
መንግሥት የዜጎችን ሰላም እና ደኅንነት የማስጠበቅ ብሎም የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሕገመንግሥታዊ ኀላፊነቱን ለመወጣትም ውጤታማ እና ተከታታይ ሕግ የማስከበር ርምጃዎችን ወስዷል ብለዋል። ምክትል ቢሮ ኀላፊው የጸጥታ መዋቅሩ የተሰጠውን ሕገ-መንግሥታዊ ተልዕኮ በመፈጸም ዘላቂ ሰላምን እና ልማትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ትግል ውድ ሕይወቱን መስዋዕት በማድረግ ሕዝባዊ ወገንተኝነቱን አሳይቷል ነው ያሉት።
ኅብረተሰቡ ከጸጥታ መዋቅሩ ጎን በመሰለፍ እያደረገው ያለውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ በማስቀጠል የተገኘውን ሰላም ማጽናት እንደሚገባውም ገልጸዋል። የሰሜን ጎንደር ዞን ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ዳኝነት ሙሉሰው የውይይት መድረኩ ላለፉት ስድስት ወራት የተከናወኑ ሕግ የማስከበር ዘመቻዎችን በመገምገም በቀጣይ ቀሪ ወራት መከናወን ያለባቸውን ተግባራት ለማቀድ ያለመ ነው ብለዋል።
ያለፋት ስድስት ወራት የጸጥታ መዋቅሩን ሥነ-ልቦናዊ፣ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ አቅም በማጎልበት እና ውጤታማ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ በመሥራት በኩል አበረታች ውጤት የታየበት መኾኑንም አስረድተዋል። በመድረኩ የተሳተፉ የጸጥታ መዋቅሩ አባላትን ጨምሮ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች የተገኘውን ሰላም በማጽናት የተጀመሩ የልማት ተግባራትን ማስቀጠል እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ደሳለኝ አበራ ባለፉት ስድስት ወራት በዞኑ በተደጋጋሚ የተደረጉ ሰላምን የማናጋት ሙከራዎች የጸጥታ መዋቅሩ ተናቦ በመሥራት ማክሸፍ መቻሉን ገልጸዋል።
በመድረኩ የተገኙት የሰሜን ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ቢምረው ካሳ የጸጥታ መዋቅሩ በአስቸጋሪ እና ፈታኝ ጊዜያት ላበረከተው ታላቅ አስተዋጽኦ ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን! .