“ተምሳሌት የኾነ የፍርድ ሥርዓት ለመገንባት እየተሠራ ነው” አቶ ዓለምአንተ አግደው

32

ባሕር ዳር: ጥር 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች ክትትል እና ቁጥጥር የሚያካሄዱባቸውን ተቋማት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም እየገመገሙ ነው። የሕግ፣ ፍትሕ እና አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚከታተላቸውን ተቋማት የሥራ አፈጻጸም እየገመገመ ነው።

የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸማቸውን ለቋሚ ኮሚቴው ያቀረቡት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው ፍርድ ቤትን ለመለወጥ የትራንስፎርሜሽን እቅድ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በሕዝብ ዘንድ ታማኝ የኾነ እና ውጤታማ የኾነ የፍርድ ቤት ሥርዓት ለመገንባት እየተሠራ ነው ብለዋል። የአማራ ክልል ተምሳሌት የኾነ የፍርድ ቤት ሥርዓት እንደነበረው የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ችግሮች ገጥመዋል፣ ይሄን ማስተካከል እና እንደ ሀገር ተምሳሌት የኾነ የፍርድ ቤት ሥርዓት መገንባት አለብን ነው ያሉት። ተምሳሌት የኾነ የፍርድ ሥርዓት ለመገንባትም እየተሠራ ነው ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ የሰው ኀይሉን የማደራጀት እና አቅምን የማጎልበት ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል። የፍርድ ቤት አሠጣጡን ለመለወጥ ቴክኖሎጂን መጠቀም እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ቴክኖሎጂን ለመጠቀም የሚያስችል ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

የፍርድ ቤት ነጻነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የሰው ኀይል አደረጃጀት ተደርጓል ነው ያሉት። የትራንስፎርሜሽን ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል። የፍርድ ቤት አማካሪ ምክር ቤትን ለማቋቋም እየተሠራ መኾኑንም አመላክተዋል።

የጸጥታ ችግሩ የዳኝነት ሥርዓቱን መፈተኑንም አንስተዋል። የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ለሥራ የተመቸ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት። የዳኝነት ተደራሽነትን የማጠናከር ሥራ መሥራቱን ገልጸዋል።

የዳኞችን እና የተሿሚዎችን አቅም የማሳደግ ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል። ቴክኖሎጂን ለመጠቀም ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ስምምነት በመፈጸም እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል። ድጋፍ የተደረጉላቸው የለሙ ሶፍትዌሮች መኖራቸውንም ተናግረዋል። የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት የትብብር መድረክ መካሄዱን የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ የጋራ እቅድ አውጥተው ወደ ሥራ መግባታቸውንም ገልጸዋል።

ፍርድ ቤቱ በአጭር ጊዜ ለውጥ እያመጣ መኾኑን ተናግረዋል። አማራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴዎችን የመጠቀም ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። የፍርድ መር አስማሚነት፣ የግልግል ዳኝነት እና ባሕላዊ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች ላይ እየሠሩ መኾናቸውን ነው የተናገሩት።

መዛግብትን እልባት የመስጠት አፈጻጸም ከባለፈው ዓመት አንጻር መጨመሩን ገልጸዋል። የዳኝነት የውሳኔ አሰጣጥ እየጨመረ እና በአጭር ጊዜ ውሳኔ የመስጠት አቅም እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

ውሳኔ የሚያገኙ መዛግብትን የመጨመር ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል። በተሠራው ሥራም ለውጥ መገኘቱንም ገልጸዋል። የዳኝነት አገልግሎት ጊዜን የመቀነስ ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል።

የመደበኛ እና የድንገተኛ ምርመራ ሥራዎችን ማጠናከር እንደሚገባም ተናግረዋል። ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም አመላክተዋል። በግማሽ ዓመቱ የሕግ ማዕቀፍ አዘጋጅተው ለምክር ቤት ማቅረባቸውን ገልጸዋል። የፍርድ ቤቶች ማጠናከሪያ አዋጅ፣ የፍትሕ እና የሕግ ኢንስቲትዩት እንደገና ማቋቋሚያ አዋጅ፣ የክልሉ የባሕል ፍርድ ቤቶች ለማቋቋም እና እውቅና ለመስጠት የተዘጋጀ አዋጅ፣ የክልሉ ተከላካይ ጠበቆች አዋጅ እና የክልሉ የዳኝነት አገልግሎት ክፍያን ለመዋስን የተዘጋጀ ደንብን ማዘጋጀታቸውን ነው ያመላከቱት።

የኅብረተሰብ እና የአጋር አካላትን ተሳትፎ የማሳደግ ሥራ ማሳደግ ላይም ሰፊ ሥራዎችን መሥራታቸውን ነው የተናገሩት።

በበጀት ዓመቱ የበጀት፣ በወረዳ ፍርድ ቤቶች የቢሮ እና የማስቻያ ቦታዎች እጥረት፣ በወቅታዊ ክልላዊ አለመረጋጋት በተወሰኑ ፍርድ ቤቶች ዳኞች ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ መኾኑን ገልጸዋል። ምክር ቤቱ ችግሮች እንዲፈቱ ድጋፍ እንዲያደርግላቸውም ጠይቀዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አሚኮ ተቋማዊ ገለልተኝነቱን እና ሙያዊ ኀላፊነቱን ጠብቆ ኢትዮጵያን ማገልገል ይኖርበታል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next articleየሕግ የበላይነት ለማረጋገጥ የኅብረተሰቡ ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡