“አሚኮ ተቋማዊ ገለልተኝነቱን እና ሙያዊ ኀላፊነቱን ጠብቆ ኢትዮጵያን ማገልገል ይኖርበታል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

40

ባሕር ዳር: ጥር 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ ከተማ ያስገነባውን ዘመናዊ ስቱዲዮ እያስመረቀ ነው፡፡ በምረቃ መርሐ ግብሩ የፌደራል እና የክልል የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ አሚኮ የአማራ ሕዝብ ምልክት ነው ብለዋል፡፡ ሀገር ወዳድ ለኾነው የአማራ ሕዝብ የሚመጥን እና በሀገር የሚወደድ ተቋም ኾኗል ነውም ብለውታል፡፡

አሚኮ ትክክለኛ፣ ወቅታዊ እና ጥራት ያለው መረጃ ለሕዝብ በማድረስ ሀገራዊ አንድነት እንዲጸና እየሠራ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የአማራ ሕዝብ ከመላ ኢትዮጵያዊያን ወንድም እህቶቹ ጋር ተንሰላስሎ እንዲኖር ቀን ከሌሊት እየሠራ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡

ይህ ዘመን በመንግሥት እና ሕዝብ የማይመሩ እና የማይገሩ ተቋማት የበዙበት ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ እውነትን ከሀሰት እየለዩ ማቅረብ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በብዛት የሚሰራጩ መረጃዎች ሕዝብን የሚጠቅሙ እና ሀገርን የሚያጸኑ ሳይኾኑ ለግል ጥቅም ሲባል የሚቀርቡ ናቸው ብለዋል፡፡ እውነትን በእውቀት ላይ ተመስርቶ ማቅረብ እንደሚያስፈልግም አንስተዋል፡፡

በዚህ ዘመን ትልቁ ፈተና አብሮነት ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ምክንያቱ ደግሞ ሀሰተኛ መረጃ ነው ብለዋል፡፡ ከዋልታ ረገጥ አስተሳሰብ ወጥቶ ሕዝብን ማሰባሰብ ላይ መሥራት እንደሚገባም አንስተዋል፡፡

አሚኮ ተቋማዊ ገለልተኝነቱን እና ሙያዊ ኀላፊነቱን ጠብቆ ኢትዮጵያን ማገልገል ይኖርበታል” ብለዋል፡፡

ርእሰ መሥተዳድሩ በመልዕክታቸው ዓለም የአማራን ሕዝብ የሚያውቀው በሚዲያ ነው ብለዋል፡፡ የአማራን ሕዝብ ትክክለኛ ማንነት፣ ባሕል፣ እሴት እና ኢትዮጵያዊ ፍቅር ለሌሎች በመግለጥ በኩል አሚኮ ኀላፊነቱን ወስዷል ነው ያሉት፡፡

ቀሪ የሀገሪቷ አካባቢዎች የአማራን ሕዝብ በእውነት እና በእውቀት ላይ ተመሥርተው እንዲያውቁ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ መስፋቱ ትርጉሙ የላቀ ነው ብለዋል፡፡

በቀጣይም መካከለኛው ምሥራቅ የአማራ ክልልን የሚያይበት መንገድ በእውነተኛ መረጃ እና በእውነተኛ ማንነቱ ላይ ተመሥርቶ እንዲኾን እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አሚኮ በተቋም ግንባታ ሂደት ውስጥ አርዓያ እና ምሳሌ ነው” አቶ ይርጋ ሲሳይ
Next article“ተምሳሌት የኾነ የፍርድ ሥርዓት ለመገንባት እየተሠራ ነው” አቶ ዓለምአንተ አግደው