“አሚኮ በተቋም ግንባታ ሂደት ውስጥ አርዓያ እና ምሳሌ ነው” አቶ ይርጋ ሲሳይ

39

ባሕር ዳር: ጥር 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ ከተማ ያስገነባውን ዘመናዊ ስቱዲዮ እያስመረቀ ነው፡፡

በምረቃ መርሐ ግብሩ የፌደራል እና የክልል የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል፡፡ በመርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የርእሰ መሥተዳድሩ የሕዝብ ግኑኝነት አማካሪ እና የአሚኮ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ይርጋ ሲሳይ አሚኮ የአማራ ሕዝብ ሀብት ቢኾንም አገልግሎቱ ግን የመላው ኢትዮጵያ ነው ብለዋል፡፡

አሚኮ የኢትዮጵያ ድምጽ ነው ያሉት አቶ ይርጋ ሲሳይ አሚኮ የሁሉም ሕዝብ ዐይን እና ልሳን ነው ብለውታል፡፡ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሚያውቀው ባለፉት ዓመታት የአማራ ክልል በርካታ ችግሮች ገጥመውታል ያሉት የቦርድ ሰብሳቢው ከፈተና በላይ ኾኖ እና ችግሮችን ተቋቁሞ በመጓዝ አሚኮ ምሳሌ ኾኖ እና ብቻውን ቆሞ የሚሠራ ነው ብለውታል፡፡

አሚኮ አሠራሩ እና አደረጃጀቱ ዘመኑን የዋጀ እንዲኾን በማድረግ ሂደቱን ሳያቋርጥ እየሠራ መኾኑንም የቦርድ ሰብሳቢው አንስተዋል፡፡ የአሚኮ የተቋም ግንባታ ለሌሎች ምሳሌ ነው ያሉት አቶ ይርጋ ሲሳይ “አሚኮ በተቋም ግንባታ ሂደት ውስጥ አርዓያ እና ምሳሌ የኾነ ተቋም ነው” ብለዋል፡፡

በሠራተኞቹ እና በመሪው መካከል የአመለካከት፣ የክህሎት እና አፈጻጸም ልዩነት በማጥበብ ተቀራራቢ አፈጻጸም እንዲኖር እየሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡ ተቋሙ በብዙ ፈተና መካከል እያለፈ ያለ ተቋም ነው ያሉት የቦርድ ሰብሳቢው በፈተና ውስጥ እያለፈም የሀገረ መንግሥት ግንባታው በፅናት እንዲቆም የፈጠረው አቅም እና ውለታ የሚረሳ እና የሚዘነጋ አይደለም ብለዋል፡፡

አቶ ይርጋ ሲሳይ በቅርቡ ክልሉ በገጠመው የሰላም እጦት ችግር ተቋሙ በርካታ ፈተናዎችን እንዳለፈ አንስተው ሰላም እንዲሰፍን አመለካከት በመቅረጽ በኩል የተለየ አበርክቶ ነበረው ብለዋል፡፡ የአማራ ክልል ሕዝብ ለሰላም የሚሠራ እና ሰላምን የሚሻ ሕዝብ መኾኑን ለሌሎች በማሳየት በኩል አሚኮ የተለየ ሚና ነበረውም ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያዊ ወግ፣ ባሕል እና እሴት ተጠብቀው ለትውልድ እንዲቀርብ በማድረግ በኩል ሚናው የጎላ እንደነበርም አንስተዋል፡፡ በቀጣይም የቀጣናው ዐይን እና ጆሮ ኾኖ የሚታመን እና የሚደመጥ የሚዲያ ተቋም እንዲኾን በቅርበት መቅረጽ ይገባል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አሚኮ ከትንሹ ጀምሮ በትልቁ የሚሠራ ተቋም ነው” ሙሉቀን ሰጥዬ
Next article“አሚኮ ተቋማዊ ገለልተኝነቱን እና ሙያዊ ኀላፊነቱን ጠብቆ ኢትዮጵያን ማገልገል ይኖርበታል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ