
ባሕር ዳር: ጥር 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሚድያ ኮርፓሬሽን በአዲስ አበባ ያስገነባውን የሚዲያ ማሰራጫ እያስመረቀ ነው። የአሚኮ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ሙሉቀን ሰጥዬ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ለታደሙ እንደግዶች ወደ ተቋማችሁ እና ወደ ሚዲያችሁ እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋል።
ዋና ሥራ አሥፈጻሚው አሚኮ ከ30 ዓመት በፊት በበኩር ጋዜጣ ሥራውን እንደጀመረ ተናግረዋል። በአማርኛ የተጀመረው የጣቢያ ስርጭት አሁን ላይ የምልክት ቋንቋን ጨምሮ በ12 ቋንቋ ስርጭቱን እያከናወነ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት።
አሚኮን የብዝኀ ልሳን እና የብዝኀ ተቋም ለማድረግ እየተሠራ እንደሚገኝም አብራርተዋል። ዜና ሠርቶ ለኢትዮጵያ ሬዲዮ በመስጠት የጀመረው አገልግሎት አሁን ላይ ዛሬ ለምረቃ የበቃውን የሬድዮ ጣቢያ ጨምሮ ሰባት ጣቢያዎችን ወደ አገልግሎት ማስገባቱን ጠቁመዋል።
በቅርቡ ደግሞ ስምንተኛ ጣቢያውን ሰቆጣ ላይ ለማስጀመር ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።አብዛኛውን የኢትዮጵያ አካባቢ ማገልገል የሚቻለው በሬዲዮ ነው ብሎ የሚያምነው አሚኮ ይህንንም ታሳቢ አድርጎ እየሠራ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።
አሚኮም ኾነ ባለቤቱ የአማራ ሕዝብ እና መንግሥት ለብዝኅነት ቅድሚያ የሚሰጡ ናቸው ያሉት የአሚኮ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ሙሉቀን ሰጥየ ይህንንም ታሳቢ ተደርጎ እየተሠራ ስለመኾኑ አብራርተዋል።
አሚኮ በጋዜጣ ብቻም በሦስት ቋንቋዎች ተደራሽ እየኾነ ስለመኾኑ አስገንዝበዋል። በአዊ ቋንቋ ቸርቤዋ፣ በኽምጣና ቋንቋ ኽምጣዊከ፣ በአፋን ኦሮሞ ደግሞ ሂርኮ በሚል ታትመው ለሕዝቡ ተደራሽ እየተደረጉ ስለመኾኑ አስገንዝበዋል።
ከቴሌቪዥን አኳያ በአንድ ቋንቋ ብቻ ማገልገል ስለማይቻል ሌሎችን ቋንቋዎችንም ተደራሽ ለማድረግ አሚኮ ኅብር እውን ኾኖ እየተሠራ ስለመኾኑ አብራርተዋል።
በተለይም ጣቢያው ገዥ ትርክትን በማስረጽ፤ ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትን ለማስፋት አጋዥ ለመኾን እየሠራ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት።
አሚኮ ከክልሉ ውጭ ያሉ ወንድሞችም በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው አገልግሎት እንዲያገኙ ሠፊ ሥራ እየሠራ እንደኾነም ጠቁመዋል።
አሚኮ በተለይ ጉምዝኛ፣ ትግርኛ፣ አፋርኛ፣ ኦሮምኛ እና ሱማሌኛ ለሀገር ውስጥ ታዳሚያን መረጃ እያደረሰ ሲኾን በሌላ በኩል ለውጭ ታዳሚያን በአረብኛ እና በእንግሊዝኛ ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋመል። ለዲፕሎማሲ ሥራውም የመረጃ ምንጭ ኾኖ እያገለገለ እንደሚገኝም አስገንዝበዋል።
በሌላ በኩል የዲጅታል ሚዲያው ላይ ለብሔራዊ ጥቅም አጋዥ የኾኑ ሥራዎችን መሥራት እንዳለበት ታሳቢ ተደርጎ እየተሠራ እንደሚገኝም ነው ያብራሩት።
ሁሉንም አካባቢዎች ተደራሽ ማድረግ እና የብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ ከአራት ከተሞች ላይ ዜና እያቀረበ ስለመኾኑም አብራርተዋል። ባሕር ዳር፣ ደሴ፣ ጎንደር እና አዲስ አበባ ላይ በማሰራጨት የተሻለ ተደራሽ ለመኾን እየሠራ ስለመኾኑም አብራርተዋል።
ዛሬ የተመረቀው ስቱዲዮ ከቀደመው ይልቅ የበለጠ ለማገልገል ያለውን ፍላጎት የሚያሳይ እንደኾነም ተናግረዋል። አሚኮ ከትንሹ ጀምሮ በትልቁ የሚሠራ ተቋም መኾኑንም ተናግረዋል። አሚኮ በሌሎች ክልሎችም ስምሪት ሰጥቶ እየሠራ ያለ ተቋም መኾኑን የተናገሩት የአሚኮ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ሙሉቀን ሰጥዬ አሁን ላይ 30 ዓመቱን እያከበረ ነውም ብለዋል፡፡
አሚኮ 60 ዓመቱን ሲያከብር ግዙፍ ተቋም እንዲኾን ታሳቢ ተርጎ እየተሠራ እንሚገኝም ጠቁመዋል፡፡ አሁን የተመረቀው ስቱዲዮ ለገዥ ትርክት ግንባታ፣ ለሀገራዊ አንድነት እና ለሁለንተናዊ ብልጽግና እንደሚያገለግል አስገንዝበዋል፡፡
አሚኮ ከአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር 4ሺህ 400 ካሬ ሜትር ቦታ ለዘመናዊ የሚዲያ ተቋም መገንቢያ መረከቡንም ጠቁመዋል፡፡ ሕንጻውን ደረጃውን ጠብቆ ለማስገንባት በሂደት ላይ ስለመኾኑ ነው የተናገሩት፡፡ አቶ ሙሉቀን ተቋሙ የተሻለ የመረጃ ሥርጭት እንዲኖረው አስፈላጊውን እገዛ እያደረገ ላለው የክልሉ ሕዝብ እና መንግሥት ምሥጋና አቅርበዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!