
ባሕር ዳር: ጥር 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጥራቱን እና ተደራሽነቱን የበለጠ ለማሳደግ በአዲስ አበባ ከተማ ዘመናዊ ስቱዲዮ እያስመረቀ ነው።
በዕለቱ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ አሚኮ ለሕዝቡ ትኩስ መረጃዎችን እየሰጠ ያለ ትልቅ የሕዝብ ተቋም ነው ብለዋል።
በ12 ቋንቋዎች ለሕዝቡ ትኩስ እና እውነተኛ መረጃ በማድረስ በኩል አርዓያ ሊኾን የሚችል ተቋም እንደኾነም ገልጸዋል። ተቋሙ ለሕዝቡ የሚበጁ እና የሚያስተምሩ ፕሮግራሞችን በማስተላለፍ በኩልም ትልቅ ሥራ እየሠራ ያለ ነው ብለዋል።
ቋንቋዎችን እንደ መሳሪያ በመጠቀም ለሕዝቡ ጠቃሚ እና ትኩስ መረጃዎችን እያደረሰም ይገኛል ነው ያሉት። ተቋሙ ሌሎች ተቋማትም በተሞክሮነት ሊወሰዱ የሚገቡ የአሠራር ሥርዓቶች ያሉት እንደኾነም ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።
አሚኮ የስርጭት አድማሱን እያሰፋ እና እያደገ ያለ ተቋም መኾኑንም ገልጸዋል። ዛሬ ላይ በአዲስ አበባ እያስመረቀው ያለው ስቱዲዮም የበለጠ ለኅብረተሰብ ለውጥ ይተጋ ዘንድ አቅም የሚኾን እንደኾነ ገልጸዋል።
በመጨረሻም አሚኮ ከዚህ በፊት የነበረውን ጥንካሬ የበለጠ በማሳደግ እና ለኅብረተሰቡ ሁነኛ ድምጽ ለመኾን እያደረገ ያለውን ተግባር ማስቀጠል እና ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!