የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ማጠቃለያ።

162

ባሕር ዳር: ጥር 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ለቀናት ሲካሄድ የሰነበተው የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ተጠናቅቋል።

የጉባኤውን ማጠቃለል አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ሁለተኛው ጉባኤ በድል መጠናቀቁን ስንገልጽ በታላቅ ኩራት ነው ብሏል። ሁለተኛ ጉባኤ የፓርቲው መሪዎች እና አባላት በሕልም ጉልበት እየተመሩ እዳን ወደ ምንዳን ለመቀየር እና ለሀገራችን እምርታዊ እድገት ማስመዝገብ የሚያስችል የአስተሳሰብ እና የተግባር አንድነት ልቆ በታየበት፣ የሕግ፣ የፍትሕ እና የዲሞክራሲ ተቋማት ነጻነት እና ገለልተኝነት በተረጋገጠበት፣ የኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት እድገት ባስመዘገበችበት፣ ከመሽኮርመም ዲፕሎማሲ በመላቀቀ የሀገራችንን ሁለንተናዊ ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብር የዲፕሎማሲ አውድ በተፈጠረበት የተካሄደ መኾኑ ታሪካዊ እና ልዩ ያደርገዋል ነው ያለው።

መደበኛ ጉባዔው ከመካሄዱ አስቀድሞ የቅድመ መደበኛ ኮንፈረንሶች መካሄዳቸውንም አስታውሷል። የጉባዔው ሂደት እና ውጤት ዲሞክራሲን በሚያረጋግጡ፣ ሁሉም የፖለቲካ ሥራዎች በተሻለ ጥራት እና ብቃት ተከናውነዋል ብሏል።

በቀጣይ ጊዜያት ያመለጡንን በሚያካክስ መንገድ በሁሉም ዘርፎች እምርታ ለማምጣት መግባባት ፈጥረናል ብሏል በመግለጫው። ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት ዓመታት በሁሉም ዘርፍ ያስመዘገባቸው ድሎች ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገሩ የእኛን ዘመን አመራር እና መፍትሔ የሚሹ ጉድለቶች ደግሞ እንዲታረሙ በመተማመን እና የላቀ ተስፋ በመሰነቅ ባለ ስምንት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተናል ብሏል።

1.የመጀመሪያው ጉባዔያችን ለጠንካራ ፓርቲ ግንባታ ልዩ ትኩረት የሰጠው ጠንካራ ፓርቲ ለውጤታማ መንግሥት እና ለጠንካራ ሀገር ግንባታ ያለውን ፋይዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው። ስለኾነም በሁለተኛው ጉባዔያችን የዚህን ውሳኔ አፈጻጸም ስኬቶች እና ጉድለቶች በጥሞና ገምገማናል። ባለፉት ሦስት ዓመታት የጠንካራ ፓርቲ ግንባታ ግባችን ለማሳካት ታልመው የተፈጸሙ የፖለቲካ እና የአደረጃጀት ሥራዎች ፓርቲያችንን ከእድሜው የቀደመ የውጤት እና የእድገት ምዕራፍ ውስጥ እንዲገኝ ማድረጋቸውን አይተናል። ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በትብብር እና በፉክክር መካከል ሚዛን በመጠበቅ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ባሕል ለመቀየር ያሳየነው ቁርጠኝነት ለሌሎች ሀገራትም ተሞክሮ እንደሚኾን ተመልከተናል። ይህም ሁሉ በቅድመ ጉባኤ ኮንፈረንሶቻችን እና በጉባዔዎቻችን አማካኝነት ባካሄድናቸው ውይይቶች ጠንካራ፣ ጤነኛ እና ውጤታማ ፓርቲ የመገንባት አጀንዳ ቋሚ ትግል የሚጠይቅ መኾኑን ተገንዝበናል።

በዚህም ምክንያት የውስጠ ፓርቲ ዶሞክራሲያችንን በማጎልበት የአደረጃጀቶቻችንን ሁለገብ ተፅዕኖ አድማስ በማስፋት፣ የአሠራር ሥርዓቶቻችንን የበለጠ በማዘመን እና የኢንስፔክሽን እና የሥነ ምግባር ኮሚሽናችንን በየደረጃው ማጠናከር እንደሚገባ አምነናል። በዚህም ጉድለቶችን እና ብልሽቶችን የማረም አቅም ያለው ሀገራዊ የመንግሥት ኢኒሼቲቮችን በሀሳብ የሚመራ እና የሕዝብ ንቅናቄዎችን በብቃት የሚያስተባብር ጠንካራ ፓርቲ ለመፍጠር የጋራ አቋም ወስደናል።

በመኾኑም በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የመሪዎቻችን እና የአባላቶቻችን ብቃት እና ጥራት በሥልጠና እና በተከታታይ ውይይቶች በማሳደግ በአስተሳሰብ እና በተግባር ብልጽግና የኾኑ፣ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በውጤታማነት እየፈጸሙ የሕዝቡን ሕይወት የሚለውጡ፣ በሥራ እና በመኖሪያ አካባቢያቸው የጠንካራ የሥራ ባሕል እና የመልካም ሥነ ምግባር መገለጫ የኾኑ፣ የኢትዮጵያን ሕልም እውን የሚያደርጉ መሪዎችን እና አባላትን በማፍራት በብቃት የለውጡ ሞተር እንዲኾኑ በማድረግ በላቀ ውጤት የሚገለጥ ጠንካራ ፓርቲ ለመገንባት የምንሠራ ይኾናል። ጠንካራ ፓርቲ ለመገንባት እንዲቻል አባላትን ለማጥራት የሚያስችል ውጤታማ የምዘና እና የግምገማ ሥርዓት እንዲዘረጋ ፣ የሥነ ምግባር እና የሞራል ዝቅጠት ተጠቂ በኾኑ መሪዎች እና አባላት ላይ የማረም ተግባር እንዲከናወን፣ አዳዲስ አባላትን የመመልመል ሥራ በጥራት እና በብቃት እንዲፈጸም እንደምናደርግ እናረጋግጣለን። ጠንካራ ፓርቲ ለመገንባት እንዲቻል ዘመኑን ማላመድ የሚያስችሉ የሀሳብ እና የታሪክ ውህደት በመፍጠር መዋቅራዊ ልሕቀት በማረጋገጥ የፖለቲካ ስክነትን እውን በማድረግ የውጤት ዘላቂነትን በቁርጠኝነት ለመፈጸም ዳግም ቃል እንገባለን።

2. የተቋማት ግንባታ ስኬት ለውጤታማ ሀገረ መንግሥት ግንባታ በእጅጉ ወሳኝ ነው ብለን ከልብ እናምናለን። ከዚህ ጽኑ እምነት ተነስተንም ዲሞክራሲን ተቋማዊ እና ሕዝባዊ ባሕል በማድረግ የሀገረ መንግሥት ቅቡልነትን በማረጋገጥ ወደ ተጨባጭ ሥራ ገብተናል። የተጀመረውን የተቋማት ሪፎርም በየዘርፉ እና በየደረጃው አጠናክረን በማስቀጠል እና ነጻ ገለልተኛ እና ብቃት ያላቸው ተቋማትን በማብዛት የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሥራችንን በጠንካራ መሠረት ለማቆም እና ጠንካራ የዲሞክራሲ ባሕል ለመፍጠር አበክረን የምንሠራ ይኾናል።

ፓርቲያችን የሚመራው መንግሥት ባለፉት ሦስት ዓመታት ልዩ ልዩ ሀገራዊ የዲሞክራሲ ተቋማትን እና የሀገር ደህንነት እና ሉዓላዊነት የሚጠብቁ ተቋማትን አቅም፣ ብቃት እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ባሕል ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር የሀገራችንን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት የማስጠበቅ አስደናቂ ውጤት ማስመዝገቡን ጉባዔያችን በስኬት ተመልክቷል።

እነዚህ ተቋማቶቻችን አስተማማኝ የሀገር ጋሻ እና መከታ ኾነው እንዲገነቡ እና ነጻነታቸው ተጠብቆ እንዲቀጥል በሙሉ ልብ እንደግፋለን። ከዚህ ጋር ተያይዞ የሕዝባችን ፍትሕ የማግኘት መብት በተሟላ መልኩ እንዲረጋገጥ የፍትሕ ሥርዓቱን የማዘመን፣ ብቁ ባለሙያዎችን የማፍራት፣ ፈጣን እና አስተማማኝ አገልግሎት እንዲሰጥ የማስቻል፣ የዳኞች ነጻነትን እና ተጠያቂነትን በሚዛን የማረጋገጥ ተግባራት እንዲከናወኑ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንታገላለን።

3. ሕልማችን ኢኮኖሚያዊ ለሉዓላዊነትን እውን በማድረግ የሀገራችንን ብልጽግና ማረጋገጥ ነው። ረጅም በማይባል ጊዜ ውስጥ ጠንካራ እና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ የገነባች ሀገር ማየት በእጅጉ እንሻለን። ሕልማችን ሁለንተናዊ ብልጽግና የተረጋገጠባት እና አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት ለመኾን የበቃች እና ዓለማቀፍዊ ተጽዕኖ አድማሷ የሰፋ ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ነው። በጉባዔያችን ኾነ በቅድመ ጉባኤ ኮንፈረንሶቻችን ሕልማችን እውን ይኾን ዘንድ እያንዳንዳችን ለኢትዮጵያ ብልጽግና በላቀ ተነሳሽነት እና ቁርጠኝነት መሥራት እንዳለብን ከልብ ተግባብተናል።

ለኢኮኖሚ ብልጽግና ግቦቻችን በጋራ በመቆም የኢኮኖሚያችን ነባር አቅሞች የሚያዳብር፣ ወደ አዳዲስ ዘርፎች የሚሻገር እና ወደ መጪው ዘመን የፈጠራ ኢኮኖሚ የሚያስፈነጥር እንዲሆን በውጤታማነት ለመታገል ወስነናል። ዘላቂ የልማት ፋይናንስ ሥርዓት በመፍጠር ሀገራችንን ከብድር ጫና የሚያላቅቅ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችሏትን አቅጣጫዎች አስቀምጠናል።

ገቢ የመሰብሰብ አቅማችንን በማጎልበት የሕዝባችንን አዳጊ ፍላጎት ለመመለስ በቁርጠኝነት እንሠራለን። የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራሞቻችንን ወደ ቋሚ ሕዝባዊ ባሕልነት እንዲሸጋገር፣ የሕዝባችን ተሳትፎ ከፊት ኾነን ለመምራት ጠንካራ አቋም ወስደናል። በመኾኑም በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የተቃና የኢኮኖሚ ማዕቀፍ በመገንባት ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝም፣ ማዕድን እና ዲጂታል ኢኮኖሚ ልማት ተደምሮ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር በማምጣት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ ያስችል ዘንድ በመፍጠር፣ በመፍጠን እና በማላቅ እንሠራለን።

4. ብልጽግና ማኅበረሰቡ ሁለንተናዊ ደህንነቱ እና ክብሩ ተጠብቆለት ማኅበራዊ መስተጋብሩም ለሀገር ግንባታ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ለማስቻል ሁለንተናዊ ብልጽግናን የሚያረጋግጥ አካታች ማኅበራዊ ልማት ዓላማን ይዞ በቁርጠኝነት እየሠራ ይገኛል። ይሄን ለማረጋገጥ ጥራት ያለው ትምህርት ለትውልድ፣ ሁለንተናዊ ልሕቀት ግብዓት ወሳኝ መኾኑን ያምናል።

በሽታን ቀድሞ መከላከል እና አክሞ ማዳን ለጤናማ እና አምራች ትውልድ ግንባታ ያለውን ፋይዳ በጥልቀት ይገነዘባል። በዚህ ምክንያት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በፓርቲያችን ፕሬዝዳንት ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አነሳሽነት ትምህርት ለትውልድ የሚል ፕሮግራም ተቀርጾ በ2016 እና 2017 ዓ.ም ብቻ 39 ቢሊዮን ብር የሚገመት የሕዝብ ተሳትፎ ለትምህርት ዘርፍ ልማት አውሏል። በፓርቲያችን የሚመራው መንግሥት አዲስ የትምህርት ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ ወደ ተግባር ገብቷል። ይህንኑ ወደ ተጨባጭ ውጤት ለመቀየር የትውልድ እሴት ግንባታ ሥራዎቻችን አጠናክሮ ለማስቀጠል፣ ትውልዱ መቻቻልን፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን፣ ወንድማማችነትን እና እህታማማችነትን፣ አርበኝነትን እየተማረ እንዲያድግ የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመሥራት የሚረዳ ሀገራዊ የድርጊት መርሐ ግብር ቀርጸን የምንቀሳቀስ ይኾናል።

በጤና ዘርፉም የጤና መድኅን ተጠቃሚዎችን የማበራከት፣ ሆስፒታሎችን እና የጤና ጣቢያዎችን የማስፋፋት ሥራዎችን ጨምሮ አመርቂ የጥራት እና የተደራሽነት የማሻሻያ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ጉባዔያችን ተመልክቷል። በተጨማሪም ፓርቲያችን ሰው ተኮር ባሕሪውን መሠረት በማድረግ የሕጻናትን እና አረጋውያንን ሁለንተናዊ መብት እና ጥቅም የሚያስከብር፣ የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ መብት፣ ክብር እና ደህንነት የሚያስጠብቁ፣ አቅመ ደካሞችን እና ለችግር ተጋላጭ የኾኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የሚደግፉ ሥራዎች በውጤታማነት መሠራታቸውን አረጋግጧል።

የወጣቶች እና የሴቶች ክንፎቻችንም ከመቸውም ጊዜ በላቀ ደረጃ በማጠናከር ወጣቶች እና ሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነታቸው ከማረጋገጥ አኳያ ከፍተኛ መሻሻል መታየቱን አይተናል። በመኾኑም እነዚህ የጀመርናቸው የማኅበራዊ ልማት ሥራዎቻችን፣ የእድገት እና የፍትሐዊነት ግቦቻችንን የሚያሳካ እና ማኅበራዊ ብልጽግናና በሚያረጋግጥ መልኩ በከፍተኛ ቁርጠኝነት አጠናክረን እናስቀጥላለን።

5. ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከር እና የሀገረ መንግሥት ግንባታችን እንዲሳካ ነጣጣይ ትርክቶች ተሸንፈው፣ አስተሳሳሪ ትርክት የበላይነት ማግኘት እንዳለበት እናምናለን። ብሔራዊ ገዢ ትርክት በልሂቃን እና በሕዝቡ ዘንድ እንዲሰርጽ እና ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን እንዲጠናከር እንሠራለን።
ይህንንም የበለጠ ለማሳካት በማኅበረሰባችን መካከል መግባባትን የሚፈጥሩ ልዩ ልዪ ሕዝባዊ ውይይቶች በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች እና በሁሉም አማራጭ መንገዶች እንዲከናወኑ እናደርጋለን። በተለያዩ ማኅበረሰቦች መካከል የሕዝብ ለሕዝብ ውይይቶችን በማድረግ ብሔራዊ ገዢ ትርክት እንዲሠርጽ እና በሕዝቦች መካከል ትስስር እና ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲፈጠር እንሠራለን።

የሚዲያ ነጻነት እና ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብት እንዲጠበቅ ኾኖ አፍራሽ ተልዕኮ ይዘው ሚዲያውን ለግጭት፣ ለብጥብጥ እና ለወንጀል በሚጠቀሙ አካላት ላይ ሕግ የማስከበር ሥራ እንዲሠራ አበክረን እንታገላለን። የብልጽግና መሪዎች እና አባላት መላውን ሕዝብ በማሳተፍ ማኅበራዊ ሚዲያውን ለገዢ ትርክት ግንባታ፣ ለብሔራዊ አንድነት፣ ለዕውቀት ሽግግር እና የኢትዮጵያን እውነት ለመግለጽ እንደምንጠቀምበት ቃል እንገባለን።

6. ብልጽግና የሀገራችን ሲቪል ሰርቪስ የእድሜውን ያክል ተቋማዊ ልሕቀት ማረጋገጥ አልቻለም ብሎ ያምናል። በመኾኑም አሁን ላይ የጅምላ ሀገራዊ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም እያደረገ አይገኝም። ከዚህ ይልቅ በየደረጃው እየተተገበረ ውጤታማነቱ የተረጋገጠ ፣ ለዘመናዊ ቴክኖሎጂ አቅም መሪነት የተሳሰረ፣ ከሌብነት እና ብልሹ አሠራር የተላቀቀ፣ ሲቪል ሰርቪስ መገንባት እንዳለበት ፓርቲያችን ያምናል።

ለዚህም ተቋማዊ ባሕሪን መሠረት ያደረገ ገቢር ነበብ ሪፎርምን ለማሳከት በቁርጠኝነት እና በከፍተኛ ትኩረት እየሠራ ይገኛል። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የተጀመረው ጥረት እንደተጠበቀ ኾኖ የአግልግሎት አሰጣጥ እና የመልካም አሥተዳደር በተለያየ መልኩ የሚገለጹ ብልሹ አሠራሮች ሕዝባችንን ለእንግልት እና ለሮሮ እያጋለጡ መኾናቸውን ጉባዔያችን በዝርዝር ገምግሟል። ዜጎች የሚተማመኑበት የፍትሕ ሥርዓትን ለመገንባት፣ የተጀመረውን የፍትሕ ሥርዓት ሪፎርም ወደ ተጨባጭ ውጤት ለማሻገር ወስኗል። የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙን በፍጥነት በመተግበር የመንግሥትን የማስፈጸም እና የአግልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል ጠንካራ አቋም ወስዷል።

ሌብነትን እና ብልሹ አሠራርን ለመቆጣጠር በፓርቲያችን መሪነት በየደረጃው እና በየዘርፉ ጠንካራ ትግል ከማካሄድ በተጨማሪ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ውጤታማ የአሠራር ሥርዓት እንዲዘረጋ አቅጣጫ አስቀምጧል። ስለኾነም ውጤታማ የኾነ ገቢር ነበብ ሪፎርም ለማካሄድ እና የሕዝብ ቅሬታ ምንጭ የኾኑ አገልግሎት ሰጪ ዘርፎች ላይ በልዪ ጥናት የአግልግሎት ማስተካከያ ለማድረግ እና የሕዝቡን እርካታ ለማሳደግ ፓርቲያችን የወሰደውን ጠንካራ አቋም ለማስፈጸም ሌት ተቀን ለመሥራት ቃል እንገባለን።

7. ጉባዔያችን ባለፊት ዓመታት ፓርቲያችን በተከተለው ሀገራዊ ክብርን የሚያጎናጽፉ፣ ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ፣ የዲፕሎማሲ እና የውጭ ግንኙነት አቅጣጫ ብሔራዊ ጥቅማችንን እና ክብራችንን ከፍ ያደረጉ ሥራዎች መፈጸማቸውን በድል ተመልክቷል። ኢትዮጵያን የብሪክስ አባል ለማድረግ የተካሄደው እልህ አስጨራሽ ትግል፣ የተገኘው ውጤት የፓርቲያችን እና የመሪያችን ዘመን የዋጀ ብቃት ሕያው ማሳያ ነው።

የዘመናት የትውልድ ጥያቄ የነበረውን ዘላቂ የባሕር በር አጀንዳ በዓለም አደባባይ ተገቢ ትኩረት እንዲሰጠው ከማድረግ በተጨማሪ ጥያቄው ሰላማዊ፣ የዲፕሎማሲ መፍትሔ እንዲያገኝ እየተደረገ ያለውን ጥረት በከፍተኛ አድናቆት ተመልክተነዋል። ፓርቲያችን የቀረጻቸው የዜጎች ክብር የውጭ ግንኙነት መርሕ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ዜጎቻችን ደህንነት እና ክብር በማስጠበቅ ረገድ ያስገኘው ጥቅምም በሚገባ ተገምግሟል።

ዲፕሎማሲያችን ከመሽኮርመም እየወጣ፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም እና ፍላጎት መርሕን እና እውነትን መሠረት ባደረገ ይገባኛል ባይነት መጠየቅ እና ማስፈጸም የሚያስችሉ ተጨማሪ አቅጣጫዎችን መርምረን ትክክለኛውን መንገድ ቀይሰናል። በመኾኑም እነዚህ አቅጣጫዎች በብቃት እንዲፈጸሙ እና ዘላቂ የባሕር በር የማግኘት ፍላጎታችን ሰላማዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ምላሽ እንዲያስገኝ በሙሉ አቅማችን፣ በተገኘው የዓለም መድረክ ሁሉ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ቆርጠን መነሳታችንን እናረጋግጣለን።

8. ፓርቲያችም ዘላቂ እና አውንታዊ ሰላም የሀገራችን የሕልውና መሠረት እና የሁለንተናዊ ብልጽግናችን አይነተኛ ዋስትና መኾኑን በጥልቀት ይረዳል። በመኾኑም ብልጽግና ፓርቲ በዚህ ጉባዔው የተጀመረው አካታች ሀገራዊ ምክክር በስኬት ተጠናቅቆ የኢትዮጵያ የዘመናት የፖለቲካ ስንክሳር እንዲዘጋ በልዩነት እና በግጭቶች ዘላቂ የመፍትሔ መንገድ እንዲቀየስ፣ ከተቻለም በጋራ ራዕያችን ላይ እንዲያግባባን ሂደቱን በሙሉ ልብ ለመደገፍ ወስኗል።

በተጀመረው የሽግግር ፍትሕ ፕሮግራም ተግባራዊነት እና ስኬታማነት የሚጠበቅበትን ኀላፊነት በብቃት ለመወጣት ይሠራል። ሰላማችን እያስተጓጎሉ ከሚገኙ የታጣቂ ኀይሎች ጋር የሚደረገው ውይይት እና ድርድር ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ተጨማሪ አቅጣጫዎች አስቀምጧል። ግጭትን ለማስቀረት እና መረጋጋትን ለመፍጠር ሁሉም አመራር እና አባል በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባም ተስማምተናል። ስለኾነም ለጉባዔያችን አቅጣጫዎች እና ውሳኔዎች ተግባራዊነት ተግተን በመሥራት የሀገራችን ሰላም ለማረጋገጥ እና ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን አጠናክረን ለማስቀጠል ሁላችን በአንድነት እና በጽናት እንቆማለን።
የብልጽግና ፓርቲ ለመላው ኢትዮጵያውያንም መልዕክት እና አደራ ያስተላልፋል።

የተከበራችሁ መላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ፓርቲያችን ብልጽግና በመጀመሪያው ጉባዔው ዋዜማ ላይ በተካሄደው ፍጹም ሰላማዊ ነጻ፣ ፍትሐዊ እና ዲሞክራሲያዊ፣ ሀገራዊ እና ክልላዊ ምርጫ የጣለችሁብንን ኀላፊነት እድልም አደራም እንደኾነ ያምናል። ፓርቲያችን በምርጫ የጣላችሁበትን እና የሰጣችሁትን እምነት የሚያከብረው ሁለተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እና የኢትዮጵያን ሕልም እውን ለማድረግ በሚረዱ ሥራዎች ላይ በመረባረብ፣ ድህነት፣ ተረጅነት፣ ውርደትን ድል በመንሳት የዜጎችን ሕይወት በዘላቂነት በመቀየር፣ ጠንካራ ተቋማትን እና ሥርዓትን በመገንባት እንደኾነ ይገነዘባል።

ባለፊት ጥቂት ዓመታት ዓለምን የሚያስደምም እድገት እና መነቃቃት የፈጠርነው፣ ሀገራችን በአፍሪካ አምስተኛ፣ ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት ሦስተኛ፣ ከምሥራቅ አፍሪካ ደግሞ አንደኛ ግዙፍ ኢኮኖሚ ያላት ሀገር እንድትሆን ማድረግ የቻልነው፣ ሀገር በቀል እና የብዝኃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ልማት አቅጣጫ በተከተለ መንገድ በመኾኑ ነው። ቀድሞም ቢኾን በጀግንነት ሀገራዊ ክብራችችም ተጎናጽፈን ስናበቃ ዓለም በተመጽዋችነት የመዘገበን በራሳችን ስህተት ነው።

ዛሬ ግን ፓርቲያችን ለልጆቻችን ምንዳን እንጂ እዳን አላወርስም በሚል አቋም ቆርጦ ተነስቷል። በራሳችን ጥረት በአውደ ውጊያ ወደ ተጎናጸፍነው የክብር ማማ ተመልሰን መውጣት አለብን። ደህነት ያመጣብንን ሀገራዊ ውርደት መስበር እና ዳግም ገናና መኾን የምንችለው በእልህ፣ በቁጭት እና በአዲስ ብሔራዊ የአርበኝነት ስሜት የራሳችንን ታሪክ ለመሥራት ከታገል እና ለድል ከበቃን ብቻ ነው። ኢትዮጵያ እንድታንሠራራ የማድረግ ትልቁ ሸክም የሚወድቀው በእኛ ኢትዮጵያውያን ትክሻ ላይ ነው። ይህ ራዕይ ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ይሁንታ፣ ሙሉ ትብብር እና ጠንካራ ተሳትፎ ውጭ ለስኬት ሊበቃ አይችልም።

ፓርቲያችን ባለፊት ዓመታት የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ የወሰደውን ተልዕኮ ለማሳከት የሚመራበትን የመደመር እሳቤ መሠረት በማድረግ ያዘጋጃቸው፣ የውስጠ ፓርቲ አቅሙን ለማጎልበት የተጠቀመባቸው ያደጉ እና አሻጋሪ ሃሰቦቹን ከፓርቲ አጥር እያወጣ የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ማዕከል ባደረገ መልኩ እንዲደርስ ከፍተኛ ጥረት ያደረገው ለዚሁ ነው።

ከጉባኤ እስከ ጉባኤ ያስመዘገብናቸው ሁሉም ድሎች የተገኙትም ሕዝቡ በፓርቲያችን ላይ ባሳደረው እምነት ፣ በሰጠው ድጋፍ እና ባደረገው ተሳትፎ ልክ ነው። እስከ ቀጣዩ ጉባኤ ድረስም ሕዝቡም በሁሉም ሀገራዊ እና አካባቢያዊ አጀንዳዎች ዙሪያ በብቃት እና በስፋት ለማሳተፍ በልዪ ትኩረት እንደሚሠራ ሲያረጋግጥላችሁ በላቀ ኩራት እና ቁርጠኝነት ነው።

እኛ ብልጽግናዎች እና መላው ኢትዮጵያውያን የጀመርነው ለውጥ የሀገራችንን የቆዩ ውስብስብ ችግሮች ከመሠረቱ የሚፈታ እና ስብራቶችን የሚጠግን ነው ብለን እናምናለን። በለውጡ ሂደት እዚህም እዛም ያጋጠሙ ችግሮች እና ጉዳቶች እያመመንም ቢኾን ለውጥ የሚያልፍበትን ተፈጥሯዊ ባሕሪ በመረዳት እና መጪውን ብሩህ ዘመን በመሻት ትግላችንን አጠናክረን እንቀጥላለን።

ይሄን የትግል ጉዞ የሚፈታተኑ ፈተናዎች መኖራቸውን ተገንዝበን፣ ፈተናን ወደ እድል የመቀየር አቅማችን ተጠቅመን ሁልጊዜም ወደ ፊት እንራመዳለን። የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን ለማድረግ የጀመርነው ትግል ግቡን ይመታ ዘንድም ትናትን፣ ዛሬን እና ነገን አስተሳስረን በመመልከት፣ የወል ትርክቶቻችንን በመገንባት እና ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ጠብቀን በፍጹም የአርበኝነት መንፈስ እና ወኔ እንዘልቃለን።

በሂደቱም ጠንካራ ፓርቲ እና መንግሥት በመገንባት የወል ሕልማችን ዳር እንዲደርስ የድርሻችንን በማበርከት የሀገራችንን ቅቡልነት እና ከፍታ ከግብ እናደርሳለን። ይሄን የተቀደሰ ዓላማችንን በመደገፍ ከፓርቲያችን እና ከመንግሥታችን ጎን ለቆማችሁ በሙሉ አክብሮታችንን እየገለጽን በቀጣይም አስፈላጊውን ድጋፍ እና ትብበር ታደርጉልን ዘንድ በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን።

እኛም ክቡር ቃላችንን ወደ ባሕል በማሸጋገር ኢትዮጵያን ማጽናት ብቻ ሳይኾን ወደ ብልጽግና ማማ ማድረሳችን አይቀሬ መኾኑ እሙን ነው። በቀጣዩ ጉባዔያችን ስንገናኝ ከተሰጠን በላይ ሠርተን ከሚጠበቅብን በላይ ፈጽመን፣ ኢትዮጵያን ይበልጥ ወደ ሁለንተናዊ ብልጽግናዋ አሸጋግረን እንደሚኾን እምነታችን ጽኑ ነው። በጉባዔያችን ያየነው ተስፋ ይህንኑ ያረጋገጠ ነው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ ከተማ ያስገነባውን ዘመናዊ ስቱዲዮ እያስመረቀ ነው፡፡
Next articleአሚኮ ለሕዝቡ ትኩስ መረጃዎችን እየሰጠ ያለ ትልቅ የሕዝብ ተቋም ነው።