የቅዱስ መርቆርዮስ በዓል የማይረሳ ትዝታቸው፣ የሚጓጉለት ናፍቆታቸው።

49

ደብረ ታቦር: ጥር 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የቅዱስ የመርቆርዮስ በዓል በደብረታቦር ከተማ አጅባር ሜዳ በድምቀት ተከብሯል። በዓሉ በሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት፣ በፈረስ ጉግስ እና በሌሎች ባሕላዊ መስተጋብሮች ነው በድምቀት የተከበረው።

በበዓሉ ላይ ያገኘናቸው ታዳሚዎች በዓሉን በየዓመቱ በናፍቆት እንደሚጠብቁት ነግረውናል።

ከልጆቿ ጋር በበዓሉ ላይ ያገኘናት ሰላም ካሳው በበዓሉ የሚፈጸመው ክዋኔ፣ መዝሙሩ፣ ቅዳሴው፣ ፈረሱ፣ የወጣቶች እና የታላላቆች ጨዋታ ሁሉ ይናፍቀኛል ትላለች። በናፍቆት የምትጠብቀው በዓል በደረሰ ጊዜም በክብረ በዓሉ እንደማትቀር ነው የተናገረችው።

ወጣት ወርቃለም እሸቴም በበዓሉ ለመታደም በአጅባር ሜዳ ተገኝታለች። በዓሉን በየዓመቱ በመንፈሳዊ አገልግሎትም ታከብራለች። ”ከጓደኞቼ ጋር ሆኜ አቅሜ በፈቀደ እያገለገልኩ ደስ ብሎኝ እውላለሁ” ነው ያለችው።

ፈረሰኛ ክንዳለም በዛ በደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር የወይብላ ሰላምኮ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። በመርቆርዮስ በዓል የፈረስ ውድድር እና ትርኢት በማሳየት ከ1975 ዓ.ም ጀምረው ከፈረስ ጋር ቁርኝት እንዳላቸው ነግረውናል።

ከአቻዎቻቸው ጋር በደብር እየተጠራሩ በዓሉን ያከብራሉ። ሥነ ሥርዓቱ ለትውልድ እንዲተላለፍ ልጃቸው እና ሌሎች እያስተማሩ እና እያሰለጠኑ ነው።

ልጃቸው ወጣት ይርጋ ክንዳለም ፈረስ ግልቢያን እና ውድድርን ከአባቱ እየተማረ ፈረሰኛ መኾኑን ገልጿል። የቅዱስ መርቆርዮስ በዓልን ጨምሮ ፈረስ ውድድር በሚደረግባቸው በዓላት እና ሥርዓቶች ሁሉ እሳተፋለሁ ብሏል።

በዓሉ በፍቅር ውድድር የሚደረግበት ስለኾነ በጉጉት እንደሚጠብቀው ነው የተናገረው። በፈረስ ጉግስ እና ጦር ውርወራ ጊዜ መጎዳዳት እንዳይኖር ጥንቃቄ እናደርጋለን። በስህተት ጉዳት ቢኖር እንኳ የበዓል እና የባሕል ስለኾነ መቀያየም የለም ነው ያለው።

የቅዱስ መርቆርዮስ ታቦት ከባሕረ ጥምቀቱ አጅባር ሜዳ ተነስቶ ወደ መንበረ ክብሩ እየተመለሰ ነው። ሊቃውንቱ እየዘመሩ፣ ምዕምናን እልል እያሉ ታቦታቸውን አጅበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየቅዱስ መርቆርዮስ ታቦት ወደ መንበሩ እየተመለሰ ነው።
Next articleየብልጽግና ፓርቲ አማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ይርጋ ሲሳይ የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት!