የጉምሩክ ኮሚሽን ባለፉት 9 ወራት 7 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር የሚገመት ኮንትሮባንድ መያዙ አስታውቀዋል፡፡

502

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 26/2012 ዓ.ም (አብመድ) የኢፌዴሪ የጉሙሩክ ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በመግለጫውም የሕገ ወጥ ንግድ ተሳትፎ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መሆኑ ተመላክቷል፡፡ የጉምሩክ ኮሚሽንም በዘጠኝ ወራት አፈጻጸሙም 7 ነጥብ 7 ቢሊዮን የሚገመት በኮንትሮባንድ ወጪና ገቢ ዕቃዎች ገቢ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

ሚያዝያ 24/2012ዓ.ም ደግሞ የጉምሩክ ኮሚሽን የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን በጋራ ባቀቋቋሙት ግብረ ኃይል በድሬዳዋና ሐረር ከተማ ከፍተኛ የሆነ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን በስድስት መጋዝኖች ካከማቹ ሕገወጥ በቁጥጥር ሥር አውለዋል፡፡ ኮንትሮባንዲስቶች ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት መድኃኒት፣ ኮስሞቲክስ፣ ኤሌክትሮኒክስና ምግብና ምግብ ነክ ዕቃዎችን ከዝነው ተገኝተዋ፡፡ እነዚህን የኮንትሮባንድ ዕቃዎችና ሕገ ወጦች ለመያዝ በተደረገ ጥረት ድሬዳዋ ላይ የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉና ሌሎች ሦስት ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱም ተገልጿል፤ ከሕገ ወጦቹ የታጠቁ ኃይሎች እንደነበሩና በቁጥጥር ስር እንደዋሉም ታውቋል፡፡

ከመድኃኒቶቹ መካከል በሕክምና ባለሙያዎች ብቻ መያዝ የነበረባቸው አደጋ መድኃኒት መገኘታቸው ተመላክቷል፡፡ ከተያዙት የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መካከል የሕጻናት ምግቦች ይገኙበታል፤ በምግብ እጥረት ለተጎዱ የሚሰጡ አጋዥ ምግቦች (ፕላምፕሌት) ይገኙበታል፡፡ የጥራት ደረጃቸው ግን አልተረጋገጠም፡፡

የራስ ጥቅምን በማስቀደም የኅብረተሰብን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ግለሰቦችንም ሆነ ቡድኖችን ኅብረተሰቡ እንዲጋልጥም ተጠይቋል፡፡

ሚያዝያ 24/2012ዓ.ም የተያዘው የኮንትሮባንድ ዕቃ ሦስት ወር ጥናት ተደርጎበትና በከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሆነም ተመላክቷል፡፡ በቀጣይም በተለይም በምሥራቅ ኢትዮጵያ የተለዩ አካባቢዎች መኖራቸውም ተገልጿል፡፡

በዘመቻው የጉሙሩክ ኮሚሽን፣ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር፣ የድሬዳዋ ከተማ መሥተዳደና የሐረር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ተሳትፈዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ጽዮን አበበ -ከአዲስ አበባ

Previous articleየመቂ-ዝዋይ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶክተር) እና ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ተመረቀ፡፡
Next articleከጥራት ደረጃ በታች የሆኑ ከ2 ሺህ 500 ሜትሪክ ቶን በላይ ምርቶች ወደ ሀገር እንዳይገቡ ታገዱ፡፡