✍️ የበጋው መብረቅ

57

ባሕር ዳር: ጥር 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በቀድሞው ጅባትና ሜጫ አውራጃ በደንቢ ዮብዲ ወረዳ ዮብዶ በሚባል ቦታ ከአቶ ኬሎ ገሮ እና ከወይዘሮ ጠላንዱ ኢናቱ በዚህ ሳምንት ጥር 21 ቀን 1913 ዓ.ም ሌፍተናንት ጄነራል ጃጋማ ኬሎ እንደተወለዱ ታሪካቸው ያስረዳል። በኢትዮጵያ አርበኞች ታሪክ ጉልህ ስፍራ ያላቸው ሌፍተናንት ጄነራል ጃጋማ ኬሎ በፋሺስት ኢጣሊያ የግፍ ወረራ ወቅት በ15 ዓመት ዕድሜያቸው ከታላቅ ወንድማቸው እና ከአጎታቸው ጋር በመኾን በአርበኝነት ለመታገል መዝመታቸውን ታሪካቸው ያስረዳል። በወቅቱም በዱር በገደል እየተዘዋወሩ የጣሊያን ወራሪ ኃይል በጀግንነት ተዋግተዋል። በአርበኝነት ዘመናቸው ያደረጓቸውን ጦርነቶች በድል እንደተወጡም ይነገራል።

ከኢጣሊያ ጋር የነበረው ጦርነት በድል ከተጠናቀቀ በኋላም ሀገራቸውን በሻለቅነት፣ በብርጌድ መሪነት እና በብሔራዊ ጦር አዛዥነት በማገልገል የሌፍተናንት ጄነራልነት ማዕረግ አግኝተዋል። ሌፍተናንት ጄነራል ጃጋማ ኬሎ በሕይወት ዘመናቸው በርካታ የክብር ሽልማቶችንም ተቀብለዋል። የኢትዮጵያ የክብር ኮከብ፣ የዳግማዊ ምኒልክ፣ የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ኒሻኖች እንዲሁም የቀድሞው የቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ የጦር እና የአርበኝነት ሜዳሊያዎች ጥቂቶቹ ናቸው። ሌፍተናንት ጀነራል ጃጋማ ኬሎ በጠላት ላይ ከፍተኛ ጀብዱ ከመቀዳጀት ባሻገር በርካታ የኢጣሊያ የጦር አዝማቾችን ማርከው በመመለስ ለፋሺስቶች የኢትዮጵያውያንን ርኅራሄ ማሳየታቸውንም ታሪካቸው ይዘክራል። ሌፍተናንት ጄነራል ጃጋማ ኬሎ ሚያዝያ 01/2009 ዓ.ም እረፍተ ሞታቸው ኾኗል፡፡ በ2001 ዓ.ም “የበጋው መብረቅ” በሚል ርዕስ በሕይወት ታሪካቸው ላይ አተኩሮ ለንባብ ከበቃው መጽሐፍ መረጃውን አጠናቀርን።

✍️ የፖስታ አገልግሎት አጀማመር
ጥር 22 ቀን 1900 ዓ.ም ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የፖስታ ኅብረት አባል እንድትኾን ለኅብረቱ ደብዳቤ የፃፉት በዚህ ሳምንት ነው።
በሀገራችን የፖስታ አገልግሎት ድርጅት በ1886 ዓ.ም በአዋጅ እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡ በዚሁ ዓመተ ምህረት በነሐሴ ወር የመጀመሪያዎቹ ቴምብሮች በፈረንሳይ ሀገር ታትመው ሐረር ከተማ እንደደረሱ ታሪክ ያትታል፡፡
የታተሙት ቴምብሮች ብዛት ሰባት ዓይነት ሲኾን ዋጋቸውም ሩብ፣ ግማሽ፣ አንድ፣ ሁለት፣ አራት፣ ስምንት እና አስራ ስድስት ግርሽ ነበር፡፡

ከእነዚህ መካካል የመጀመሪያዎቹ አራቱ የዳግማዊ ምኒሊክ የዙፋን ልብሳቸውን እንደተጎናፀፉ የሚያሳዩ ሲኾን የቀሩት ሦስቱ ደግሞ የይሁዳ አንበሳን ምስል የያዙ ነበሩ፡፡
የኢትዮጵያ ፖስታ ቴምብሮች ለመጀመሪያ ጊዜ ሽያጭ ላይ የዋሉት በጥር ወር 1887 ዓ.ም በእንጦጦ፣ በሐረር እና በድሬደዋ ከተሞች ነበር፡፡

ከአንድ ዓመት በኋላ በኢትዮጵያ የመጀመሪያዎቹ ቴምብሮች በፓሪስ ከተማ በዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ በተዘጋጀው የቴምብር ኤግዚቢሽን እንዲታዩ ተደርጎ በተመልካች ዘንድ አድናቆትን አትርፈዋል፡፡ በኤግዚቢሽኑ ወቅትም ቁጥራቸው በርከት ያሉ ቴምብሮች እንደተሸጡ ይነገራል፡፡
የኢትዮጵያ የፖስታ አገልግሎት እንደ አውሮፓ ዘመን ከ1899 እስከ 1945 ዓ.ም ድረስ በፖስታ ቴሌፎን እና ቴሌግራፍ ስር ቆይቶ ቀስ በቀስ ራሱን እያሥተዳደረ በ1958 ዓ.ም እንደገና በአዋጅ እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡
በ1901 ዓ.ም ኢትዮጵያ የዓለም የፖስታ ኅብረት አባል ለመኾን በመቻሏ የኢትዮጵያ ፖስታ ቴምብሮች ለመጀመሪያ ጊዜ የሀገሪቱን ወሰን አልፈው በመላው ዓለም በሚገኙ አባል ሀገራት መሰራጨት ጀምረዋል፡፡

✍️ ማህተመ ጋንዲ
ሕንድ ከእንግሊዝ የቅኝ አገዛዝ ቀንበር ለማላቀቅ አይነተኛውን ሚና የተጫወተ እና በነፃነት ትግሉ ላይ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ የኾነ ሰው ነው ፡፡ ማህተመ ጋንዲ እንደ አውሮፖውያኑ ዘመን ከ1869 እስከ 1948 እንደኖረ ይነገራል።.ጋንዲ በሕንድ የነጻነት ታሪክ ላይ ትልቅ አሻራውን የጣለ እና በወቅቱ ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ለመላቀቅ ሲንቀሳቀስ በነበረው የሕንድ የነፃነት ንቅናቄን ይመራ የነበረ ታላቅ ሰው ነበር፡፡ ጋንዲ ሕንድን ወደ ነፃነቷ የመራ እና በሀገሪቱ የሠብዓዊ መብት እና እኩልነት እንዲሠፍን ጠንካራ ትግል ያደረገ ብርቱ ሰው ነበርም ይሉታል፡፡

ጋንዲ በሀገሩ ሕዝቦች ዘንድ ባፑ ወይም ጋንዲጂ በመባል ይጠራል፡፡ የዚህ ስያሜ ትርጉም አባት ማለት ነው፡፡ ይሄ ስያሜውም ጋንዲን የሕንድ አባት ተብሎ እንዲሞገስ አድርጎታል፡፡
ማህተመ ጋንዲ ከሚታወቅባቸው ነገሮች ውስጥ እ.ኤ.አ. በ1930 ዓ.ም. እንግሊዞች በሕንድ ሕዝብ ላይ ጥለውት የነበረውን ግብር በመቃወም ያስተባበረው ሰላማዊ ሰልፍ አንዱ እና ተጠቃሹ ነው፡፡
ከዚያ በኋላም እ.ኤ.አ. በ1942 ዓ.ም እንግሊዝ ከሕንድ ቅኝ ገዢነት እንድትለቅ እና ሕንድ ነፃነቷን እንድትጎናፀፍ በጊዜው ለእንግሊዝ መንግሥት ጥሪ አድርጓል፡፡
ይህ ታላቅ የነፃነት ታጋይ የሕንድ ባሕላዊ ልብስን በመልበስም ይታወቃል፡፡

ማህተመ ጋንዲ ሕንድን ነፃ ማድረግ የሚቻለው በብዝኀ ሃይማኖት መሠረት እንጂ በአንድ ሃይማኖት አስተሳሰብ አለመኾኑን አበክሮ ይከራከር ነበር፡፡
በመጨረሻም የጋንዲ ትግል ፍሬ አፍርቶ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1947 እንግሊዝ ቅኝ ገዥነቷን በመተው ለሕንድ ነፃነቷን አጎናጽፋለች፡፡
ይህ የሀገሪቱ የነጻነት አባት ተብሎ የሚጠራው ማህተመ ጋንዲ እ.ኤ.አ. ጥቅምት 2 ቀን 1869 በመወለዱ ምክንያት ጥቅምት 2 ቀን በሕንድ የብሔራዊ ነፃነት ቀን ተብሎም ይከበራል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ለመምህራን የመኖሪያ ቤት አገልግሎት የሚውል ሕንጻ አስገንብቶ አስመረቀ።
Next article“ዛሬ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የብልፅግና ፓርቲን ምርጫ አካሂደናል” ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)