
እንጅባራ: ጥር 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የመምህራንን የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለል በ1ኛ ዙር የግንባታ ምዕራፍ ያስገነባቸውን ሦስት አፓርትመንቶችን አስመርቋል።
አፓርትመንቶቹ ከባለ አንድ እስከ ባለሦስት መኝታ ያላቸው180 መኖሪያ ቤቶችን፣ የንግድ ሱቆችን እና ካፍቴሪያዎችን የያዙ ናቸው።
ለአፓርትመንቶቹ አጠቃላይ ግንባታ እና ለመሠረተ ልማት ዝርጋታ ከ677 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ተደርጎበታል ተብሏል።
የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጋርዳቸው ወርቁ (ዶ.ር) ለዩኒቨርሲቲው ተልዕኮዎች ስኬታማነት የመምህራን የተረጋጋ ኑሮ ወሳኝ መኾኑን ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው በመምህራን መኖሪያ ቤት ልማት ላይ እየሠራ ያለው ሥራ ይህንን ታሳቢ ያደረገ እንደኾነም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።
በዩኒቨርሲቲው በ2ኛ ዙር የግንባታ ምዕራፍ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ በሚኾን ወጭ 2 አፓርትመንቶች በግንባታ ላይ መኾናቸውን ያነሱት ፕሬዚዳንቱ ግንባታቸው ሲጠናቀቁ የዩኒቨርሲቲውን 55 በመቶ የመምህራን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ይመልሳልም ነው ያሉት።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ የተገኙት የእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ የኔዓለም ዋሴ ዩኒቨርሲቲው የመምህራንን የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለል እየወሰደ ያለው ርምጃ የሚበረታታ መኾኑን ተናግረዋል።
ከተማ አሥተዳደሩ የመምህራንን ዘላቂ የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለል ከዩኒቨርሲቲው ጋር በቅርበት እንደሚሠራም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ገልጸዋል።
የዕድሉ ተጠቃሚ መምህራንም በየጊዜው እየናረ የመጣው የመኖሪያ ቤት ኪራይ እና የመኖሪያ ቤቶች እጥረት በሥራቸው ላይ ጫና ፈጥሮ መቆየቱን ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው መኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ መስጠቱ መምህራን በሥራ ቦታቸው ተረጋግተው እንዲሠሩ እና የዩኒቨርሲቲውን ተልዕኮዎች በአግባቡ እንዲወጡ የሚያስችል እንደኾነም የዕድሉ ተጠቃሚዎች ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!