“በዓሉ ቂምን የምንሽርበት፣ ፍቅርን የምናጸናበት እና አንድነትን የምናጠናክርበት ነው” ምክትል ከንቲባ ኃይለኢየሱስ ሰሎሞን

34

ባሕር ዳር: ጥር 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የቅዱስ መርቆርዮስ ዓመታዊ ክብረ በዓል በደብረ ታቦር ከተማ በአጅባር ሜዳ እየተከበረ ነው።
በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ኃይለኢየሱስ ሰሎሞን ደብረ ታቦር ታሪክ በጥልቅ አሻራውን ያስቀመጠባት፣ የከፍታ እና የአንድነት ምልክት፣ የኢትዮጵያ ትንሳዔ የተበሠረባት፣ ዕውቀት፣ ጀግንነት፣ ጥበብ፣ ተፈጥሮ እና ታሪክ የተዋሃዱባት የአጼ ቴዎድሮስ መናገሻ ከተማ ናት ብለዋል።

ደብረ ታቦር በረጅም የታሪክ ዑደቷ በርካታ ታሪካዊ ሁነቶችን ማስተናገዷንም ገልጸዋል። ደብረ ታቦርን ታሪክ እና ተፈጥሮ ከፍታን አጎናጽፈዋታል ነው ያሉት። ደብረ ታቦር የታሪክ ማማ ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው የሀገር አንድነት የጸናበት መኾኑንም ገልጸዋል። በዘመነ መሳፍንት አንድነቷ የተፈተነችው ኢትዮጵያ አንድነቷ የጸናው በደብረ ታቦር መኾኑን ነው የተናገሩት።

ነገሥታት መናገሻ ያደረጓት፣ ጀግኖች እና ቃላቸውን የማያጥፉ የሀገር ባለውለታዎችን ያበረከተች ከተማ መኾኗንም አንስተዋል። ደብረ ታቦር የታሪክ አድባር እና የሥልጣኔ ፈር ቀዳጅ፣ የአጼ ቴዎድሮስ የቴክኖሎጂ ጥማት ማስታገሻ፣ በአፍሪካ ቀዳሚውን የኢንዱስትሪ መንደር የጀመረች፣ የሥልጣኔን መንገድ የቀየሰች፣ ብርሃን ዘ ኢትዮጵያን እቴጌ ጣይቱን ያበቀለች፣ የዘመናዊነት ኢትዮጵያ ጠንሳሽ፣ የጥበብ ምድር ናት ነው ያሉት።
በደብረ ታቦር በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል የቅዱስ መርቆርዮስ ዓመታዊ የንግሥ እና የፈረስ ጉግሥ በዓል አንደኛው መኾኑን ነው የተናገሩት። በዓሉ መንፈሳዊ እና ታሪካዊ ይዘቱን ጠብቆ ሺህ ዘመናትን የተሻገረ ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው በዓሉ ቂምን የምንሽርበት፣ ፍቅርን የምናጸናበት ፣ አንድነትን የምናጠናክርባት፣ ጥላቻን ሰብረን ፍቅር የምናንግስበት ሊኾን ይገባል ብለዋል።

የቅዱስ መርቆርዮስ በዓልን በመተሳሰብ እና በወንድማማችነት ስሜት ልናከብረው ይገባል ነው ያሉት። ኢትዮጵያ ብዙ ፈተናዎችን እየተሻገረች መቆየቷን የተናገሩት ምክትል ከንቲባው የሚገጥሙ “ፈተናዎችን የመሻገሪያው ቁልፉ አንድነት እና ወንድማማችነት ነው” ብለዋል።
አሁንም ቢኾን ችግሮች ሲገጥሙ መሻገር የሚቻለው በሰለጠነ እና ጥንቃቄ በተመላበት መንገድ በአንድነት በመቆም ነው ብለዋል። የቅዱስ መርቆርዮስ በዓል ከሃይማኖታዊ በዓልነቱ ባሻገር የሕዝብ አንድነትን የሚያጸና መኾኑን ገልጸዋል።

የቤጌምድር ቀደምት አርበኞች በፈረስ ገስግሰው፣ በጋሻ መክተው፣ የውጭ ወራሪን ጠላት በጦር ድል መትተው ሀገርን ለትውልድ ማስረከባቸውን ነው የተናገሩት። የአሁኑ ትውልድም በአብሮነት እና በአንድነት ለሀገር ሰላም መሥራት ይጠበቅበታል ነው ያሉት።
የከተማዋ ነዋሪዎች የከተማዋን ሰላም በመጠበቅ ለልማቷ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም አሳስበዋል። በአጅባር ሜዳ የሚከበረው የቅዱስ መርቆርዮስ በዓል ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ባሻገር የቀድሞ የሀገር ባለውለታዎች የሚዘከሩነት መኾኑን ነው የተናገሩት።

በዓሉ እምነት፣ ባሕል፣ ጀግንነት፣ ማንነት ደምቀው የሚታዩበት መኾኑን ነው ያነሱት። የፈረስ ጉግሥ ጨዋታ ተመራጭ መዝናኛ መኾኑን ያነሱት ምክትል ከንቲባው ለሀገራችን ትልቅ የቱሪዝም ሃብት ነው ብለዋል።
የፈረስ ጉግስ የጀግንነት አብነት መኾኑንም ገልጸዋል። ለሁሉም ነገር መሠረቱ ሰላም ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ ሰላምን እንስበክ ነው ያሉት። ተጨማሪ የልማት ሥራዎች እንዲመጡ እና ያለው እንዲሰፋ ሰላምን ማጽናት ይገባል ነው ያሉት። ሁላችንም ለሰላም እንታገልሸ፣ ለአብሮነት እንሥራ ብለዋል በመልዕክታቸው።

ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleዶክተር ዐቢይ አሕመድ የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ኾነው ተመረጡ።
Next article“በብዙ ፈተና ውስጥ ብናልፍም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነውና በዓሉን በሰላም ለማክበር ችለናል” ብፁዕ አቡነ ሚካኤል