“ደብረ ታቦር መሀል ጀግኖች የጻፉትን ሊቆች ያነቡታል አጅባር ከሜዳው ላይ ለዓለም ይገልጡታል”

57

ባሕር ዳር: ጥር 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጀግኖች አባቶች አያሌ ታሪክ ጽፈውበታል። ከተራራው የገዘፈ ታሪክ አቁመውበታል። ሊቃውንት እንደ አሸዋ በዝተውበታል። እንደ ከዋክብት ደምቀውበታል። እንደ ውቅያኖስ ጠልቀውበታል። በጥበብ የምድር እና የሰማይ ምስጢራትን ዳስሰውበታል። በጥበብ ተራቅቀውበታል።
ጎበዛዝቱ እንደ አንበሳ አግስተውበታል። እንደ ነብር ተመዘግዝገውበታል። እንደ ጀምበር አብርተውበታል። እንደ መብረቅ ጠላታቸውን አስደንግጠውበታል። ሀገር አጽንተውበታል። የአንድነትን ገመድ አጥበቀውበታል። ፍቅር ተክለውበታል። ኢትዮጵያን አስውበውበታል።
ንጉሡ በአስፈሪ ግርማ ተቀምጦበታል። ለዘመናት የሚዘከረውን ታሪክ ጀምሮበታል። የሥልጣኔን ብርሃን አብሮቶበታል። አላስተኛ ያለውን ራዕይ ገልጦበታል። ጠላት ያበዛበትን ጥበብ አሳይቶበታል።
መኳንንቱ እና መሳፍንቱ ደምቀውበታል። ታማኝ የጦር አበጋዞች በኩራት ኖረውበታል። ወይዛዝርቱ ልብን የምታስደነግጥ ውበታቸውን ገልጠውበታል። የረቀቀ ታሪክ እየተገለጠ ይነበብታል። ትውልድ ሁሉ የሚኮራበት የአበው እና የእመው ዝና ይዘከርበታል። ይነገርበታል። ሃይማኖት ይሰበክበታል። የጥንቱ እና የጠዋቱ ይጸናበታል። ባሕል እና እሴት ይጠበቅበታል። ታሪክ እና ሀገር ይሠራበታል። ጥበብ እና ምስጢር ይሸመንበታል። ጀግንነት እና ታላቅነት ከፍ ብሎ ይታይበታል።

ትናንት፣ ዛሬ እና ነገ ይጋመዱበታል። ፍቅር፣ ሰላም እና ተስፋ ይጸኑበታል። ጀግንነት፣ ሀገር ወዳድነት፣ አንድነት፣ ሩቅ አሳቢነት፣ ደግነት፣ እንግዳ ተቀባይነት ደምቀው ይኖሩበታል ማማው ደብረ ታቦር።
ማማው ደብረ ታቦር ታሪክ የሚቀዳበት የማይነጥፍ ምንጭ ነው። ሃይማኖት የሚጸናበት የማይናወጥ አለት ነው። ማማው ደብረ ታቦር ታሪክ የሚነበብበት በወርቅ የተቀለመ ብራና ነው። ማማው ደብረ ታቦር ጥበብ፣ ሃይማኖት፣ ታሪክ፣ ባሕል እና እሴት የሚኖሩበት የማያረጅ ቤተ መዘክር ነው። ማማው ደብረ ታቦር ከተራራ ላይ የተቀመጠ ራሱ ተራራ ነው።

ንጉሠ ነገሥት ቴዎድሮስ በክብር የኖረበት። የታሪክ አሻራውን ያስቀመጠበት። ቃል ኪዳኑን ያጸናበት። ለልጅ ልጅ የሚወረስ የታሪክ አደራ የሰጠበት ደብረ ታቦር ነግረው የማይጨርሱት፣ ጽፈው የማይዘልቁት እልፍ ታሪክ አለው። ከዓመት እስከ ዓመት ታሪክ ይነገርበታል። ታሪክም ይሠራበታል። ጀምበር ጠልቃ በዘለቀች ቁጥር ስብሐተ እግዚአብሔር ይደረስበታል። አምላክ ይወደስበታል።
ተራራዎች፣ አድባራት እና ገዳማት የታነጹባቸው፣ ሜዳ እና ሸንተረሮቹ ታሪክ የተሠራባቸው፣ ጎዳናዎቹ ባሕል እና ወግ የሚገለጥባቸው ናቸው። ይህ በሰርክ ታሪክ የሚነገርበት፣ ሃይማኖት የሚሰበክበት የታሪክ ማኅደር በወርሃ ጥር ይደምቃል። በበዓለ መርቆሬዎስ እንደ ፀሐይ ይሞቃል። እንደ ከዋክብት ያሸበርቃል። እንደ ጨረቃ ይደምቃል።

“ደብረ ታቦር መሀል ጀግኖች የጻፉትን ሊቆች ያነቡታል
አጅባር ከሜዳው ላይ ለዓለም ይገልጡታል” ታላቁ ሜዳ አጅባር በወርሃ ጥር ታቦታት ያድሩበታል። ሊቃውንት ይሰባሰቡበታል። የጥንቱን ታሪክ ለዓለሙ ሁሉ ይነግሩበታል። ለዓለሙ ሁሉ ይገልጡበታል። ደብረ ታቦር በበዓለ መርቆሬዎስ ከፍ ብሎ ያበራል። ከግርማ ላይ ግርማ ጨምሮ ዓለሙን ይጣራል። አጅባር የክብር ካባውን ይደርባል። የንግሥና ዘውዱን ይደፋል።

አጅባር ታላቁ ንጉሥ ቴዎድሮስ ታላቁን ጉባኤ ያደረገበት። ታላቅ ታሪክም የተሠራበት። ታቦታት የሚቀድሱት። ምዕምናን የሚባረኩበት ታላቅ ሥፍራ ነው። ንጉሡ ቴዎድሮስ በአጅባር ታላቅ የሃይማኖት ጉባኤ አስደርጎ ጉባኤው እጹብ ድንቅ ተብሎ ተጠናቅቆ ነበርና እንዲህ ተብሎ ተነገረ ይባላል።
” ለነፍሱ ሥራ ጥበበኛ የኾነ ቴዎድሮስ ጽዮንን ማደሪያው አድርጓታልና የማይደረግ ነገር ተደረገ። በታቦር ጉባኤውን ባደረገ ጊዜ የማይደረግ ነገር ተደረገ። ይሄ ጉባኤ ከተደረገማ ከዚህ በኋላ ቁስጥንጥንያ ምንድን ናት? ከዚህ በኋላ ቁስጥንጥንያ ማለት ኢትዮጵያ ናት።
ንቂያም ደብረ ታቦር ናት” ተባለ ይላሉ አበው። ንቅያን፣ ኤፌሶንን እና ቁስጥንጥንያን ከመተረክ ይልቅ ደብረ ታቦርን እና አጅባርን ንገሩ ስለ እነርሱ ተርኩ ማለታቸው ነበር። ለዚህ ነው ደብረ ታቦር ታላቅ የሚባለው። አያሌ ታሪኮችን ይዟልና።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የደብረ ልዑላን ደብረ ታቦር መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን የአራቱ ጉባኤያት መምህር መምህረ መምህራን የኔታ በጽሐ ዓለሙ አጅባር ማለት ምን ማለት ነው? ሲባሉ ሀጅ ባሕር ማለት ነው ይላሉ። በስፍራው ባሕር ነበር። ደብረ ታቦር ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ተተክሎ ታቦተ ሕጉ ወጥቶ የጥምቀት በዓልን ለማክበር ባሕሩ ያስቸግር ነበር። በዚያም ጊዜ ሊቃውንቱ ባሕሩን ብናስተነፍሰው እኮ ይሄዳል። ጥምቀቱንም በዚህ እናክብር አሉ ይባላል። ስያሜውንም ከዚያው አገኘ የሚሄድ ባሕር እንደማለት ነው ይላሉ።
አጅባር የሀገር አንድነት የጸናበት፣ ፍቅር የበዘባት፣ ታቦታት ከጥንት ዘመን ጀምሮ የሚያድሩበት፣ ምድርንም የሚባርኩበት ነው ይሉታል። እነኾ ዛሬም ታቦታት በአጅባር እያደሩ ምድርን ይባርኳታል። ይቀድሷታል።
ይህ ታሪካዊ ሜዳ አጼ ሠይፈአርድ ደብረ ታቦር ኢየሱስን አስተክለው ጥምቀተ ባሕሩን አጅባር ሜዳ እንዲኾን ካደረጉ ጊዜ ጀምሮ በታሪካዊቷ ከተማ የተተከሉ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ጥምቀተ ባሕራቸውን በአጅባር አድርገዋል ይላሉ ሊቁ። ስለ ምን ቢሉ ታሪካዊ ነውና። በአጅባር ከሌሎቹ ሁሉ በተለየ መልኩ ረዘም ላሉ ቀናት ታቦታት እየወረዱ ጥምቀት ይከበራል። ሕዝቡና ምድሩም ይባረካል። ሊቁ ሲናገሩ አጅባር የታቦታት ሁለተኛ መንበራቸው ነው። ቀደም ባለው ጊዜ ሕዝብ እንዳሁኑ ሳይሰፋ በጥምቀት ጊዜ የአጼ ቴዎድሮስ ድንኳን ይዘረጋ ነበር። በዚያም ድንኳን ሕዝብ ይሰበሰባል። ታላቁን በዓል በታላቅ ግርማ ያቀርባል።

አጅባር የንጉሥ ዳስ የተጣለበት፣ የንጉሥ ሰርግ የተሰረገበት ነው። አጅባር ነገሥታቱ በታወሱ ቁጥር አብሮ የሚወሳ ከሜዳነት የተሻገረ ታላቅ ሥፍራ ነው። አጅባር ነገሥታቱ፣ መሳፍንቱ እና መኳንንቱ ፈረስ የሚጋልቡበት፣ ልዑላኑ የፈረስ ጉግስ የሚማሩበት፣ የቤተ መንግሥቱን ትምህርት እና የጦሩን ስልት የሚያውቁበት ድንቅ ሥፍራ ነው።

በበዓለ መርቆሬዎስ ነገሥታቱ በአጅባር ሜዳ በወርቅ ወንበር ተቀምጠው ሥርዓቱን አይተዋል። በፈረስ ላይ ኾነው ለታቦቱ ክብር ሰጥተዋል። የክብሩ ተካፋይም ኾነዋል። ያ ቀደም ሲል ነገሥታት ከመሳፍንቶቻቸው ከመኳንንቶቻቸው እና ከጦር አበጋዞቻቸው ጋር የተገማሸሩበት አጅባር ዛሬም የእነርሱ የልጅ ልጆች ይደምቁበታል። ከፍ ብለው ይታዩበታል። ክብራቸውን እና ታሪካቸውን ለዓለሙ ሁሉ ይገልጡበታል።
” ማማው ደብረ ታቦር በክብር ይጠራል

አጅባር ከሜዳው ላይ ታሪክ ይናገራል” ደብረ ታቦር በክብር ይጠራል። በክብር ይኖራል። ታሪክ እና ጥበብን ይዘክራል።
እነኾ በዓለ መርቆሬዎስ ደርሷል። አጅባር ከአፍ እስከ ገደፉ በሰው ተመልቷል። እኒያ ጀግኖች ፈረሶቻቸውን ሸልመው ከመርቆሬዎስ ፊት ቆመዋል። ለክብሩም እጅ ነስተዋል። ዛሬ አጅባር በእልልታ ትዋጣለች። ደብረ ታቦርም በውዳሴ ትመላለች። በሆታ ትደምቃለች። እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ በሚሉ ፈረሶች እና ፈረሰኞች ትጨነቃለች። ደብረ ታቦር ተሞሽራ እንዳደረች ተሞሽራ ትውላለች። ተሞሽራም ትከርማለች።

ታሪክ በበዛበት፣ ሃይማኖት በጸናበት፣ ሊቃውንቱ በማይነጥፉበት፣ ሕዝብ በሚሠባሠብበት፣ ታቦታት በሚያድሩበት፣ ጀግኖች በሚመላለሱበት፣ ነገሥታት በተመላለሱበት፣ ብፁዓኑ በሚባርኩት በአጅባር ሰማይ እፁብ የሚያሰኘው ነገር ይታያል። ምድራዊ እና ሰማያዊ ሥርዓት ይፈጸማል። ሂዱ በአጅባር ተመላለሱበት። ድንቁን ነገር ተመልከቱበት

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleእናቶች ለጤና ችግር እንዳይጋለጡ የወሊድ እና የምጥ እንክብካቤን ጥራት ማስጠበቅ ይገባል።
Next articleዶክተር ዐቢይ አሕመድ የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ኾነው ተመረጡ።