“ከቀደመ ባሕላችን ጋር አስተሳስረን፣ከታሪካችን ጋር አዋሕደን፣ ከዘመኑ ጸጋዎቻችን ጋር አሰናስለን ልንጠቀምበት ይገባል” አቶ መልካሙ ፀጋዬ

48

ባሕር ዳር: ጥር 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ መልካሙ ፀጋዬ ለቅዱስ መርቆርዮስ ዓመታዊ ክብረ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም የአማራ ክልል ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋገሩ በእኛ ዘመን የደረሱ ታይተው የማይጠገቡ፣ ተነግረው የማያልቁ አያሌ ቱባ ባሕላዊና ሃይማኖታዊ ትውፊቶች አሉት ብለዋል።

በክልሉ ከሚገኙ ውብና ማራኪ ባሕላዊ ሁነቶች መካከል አንዱ የፈረስ ጉግስ በቀደመ ነገሥታት ዘንድ እጅግ ተወዳጅ የነበረና ለትውልድ የተሸጋገረ መኾኑን ነው ያመላከቱት።

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ያለፉ ነገሥታት በየዘመናቱ ሀገራችንን ለመውረር ከመጡት የውጭ ጠላቶች ጋር ያደረጉትን ተጋድሎ በድል የተወጡትና ለንግሥና የበቁት በፈረሶቻቸው ታግዘው እንደኾነም ከታሪክ እንረዳለን ነው ያሉት።

ፈረስ በየትኛውም ዘመን ቢኾን የነገሥታት የክብር መገለጫ እና ጌጥ ሆኖ ዘመናትን ተሻግሯል ብለዋል። ለዚህም ነገሥታቱና መኳንንቱ በፈረሶቻቸው ፈረሶቻቸውም በነገሥታቱና በመኳንንቱ ይጠሩ ነበር ነው ያሉት።

የታሪክ ማህደር የነገሥታት ማረፊያቸው ጥንታዊ እና ባሕላዊ እሴቶቻችን መገኛ በሆነችው ደብረታቦር ከተማ በየዓመቱ የፈረስ ጉግስ ትርዒት በሰማዕቱ የቅዱስ መርቆሪዮስ የመታሰቢያ ዕለት ጋር አብሮ ይከወናል ብለዋል።

በ1840ዎቹ አካባቢ እንደተጀመረ የሚነገርለት የጥንታዊቷ ከተማ መገለጫ ጌጥ፣ ውበቷ እና ትውፊቷ የፈረስ ጉግስ ጨዋታ በራስ ጉግሳ ወሌ ዘመን ከቅዱስ መርቆሪዮስ መታሰቢያ በዓል ጋር እንዲገናኝ ተደርጎ እየተከበረ ለዚህ ዘመን ትውልድ መድረሱንም አመላክተዋል።

በዚህ የፈረስ ጉግስ ጨዋታ ፈረሱን፣ ፈረሰኛውን እና ታዳሚውን የሚያገናኝ እጅግ ለስሜት የቀረበ አስደሳች ክስተት አለ ብለዋል። እሱም ፈረሱ ለባለቤቱ ሲጫወት፣ ፈረሰኛው በፈረሱ ብርታትና ታዛዥነት ጉግሱን ሲያካሂድ ታዳሚው ደግሞ በስሜት ከፈረሱም ከፈረሰኛውም ጋር አብሮ በስሜት ይጫወታል ነው ያሉት።

በዚህ የፈረስ ጉግስ ጨዋታ ሌላኛው ክስተት በቡድን ሆነው በውድድር መንፈስ ጦር እየተወራወሩ ሲጫወቱ የዋሉት ፈረሰኞች ጨዋታው ካለቀ በኋላ የአሸናፊም ሆነ የተሸናፊነት መንፈስ ሳይኖር በአንድነት አብረው የሚዘልቁበት ኹነት ነው።

ይህ ሁነት ድንቅ ነው ያሉት ኀላፊው ከእኛ አልፎ ለውጭ ጎብኝዎች መዳረሻ የሚኾን ነው ብለዋል። ከቀደመ ባሕላችን ጋር አስተሳስረን፣ከታሪካችን ጋር አዋሕደን፣ ከዘመኑ ጸጋዎቻችን ጋር አሰናስለን በማልማት እና የቱሪስት መዳረሻ በማድረግ ልንጠቀምበት ይገባል ነው ያሉት።

ሁላችንም እንደዜጋ እነዚህን ቱባ ባሕላዊ ሀብቶች ከመጠበቅ ባለፈ ለዓለም በማስተዋወቅ ትልቅ የቱሪዝም መስህብ ለማድረግ እና የኢኮኖሚ ምንጭ እንዲሆኑ ለማስቻል በትኩረት ልንሠራ ይገባል ብለዋል።

እንኳን በፈረስ ጉግስ ታጅቦ ለሚከበረው ለቅዱስ መርቆርዮስ ዓመታዊ ክብረ ዓል አደረሳችሁ ነው ያሉት በመልዕክታቸው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአጅባር ሜዳ እና የፈረስ ጉግስ ታሪክ!
Next articleእናቶች ለጤና ችግር እንዳይጋለጡ የወሊድ እና የምጥ እንክብካቤን ጥራት ማስጠበቅ ይገባል።