የአጅባር ሜዳ እና የፈረስ ጉግስ ታሪክ!

189

ባሕር ዳር: ጥር 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ፈረስ በተፈጥሮ ካለው ባህሪ አንጻር በደጋማው ክፍል የሚኖር እንስሳት ነው፤ ደቡብ ጎንደር ዞን ደግሞ በርሃ፣ ቆላ፣ ወይና ደጋ እና ደጋ የአየር ጸባይን የያዘ የሀገራችን ክፍል ነው።

ደጋማው ክፍል ላይ የሚበቅሉ እፅዋቶች እንዳሉ ሁሉ ደጋማ አካባቢ የሚመቻቸው እንስሳትም አሉ። ደጋን ከሚመርጡ እንስሳቶች ውስጥ ደግሞ ፈረስ አንዱ ነው።

በደቡብ ጎንደር ዞን ደጋማ አካባቢዎች በተለይም በጉና ተራራ አቅራቢያ በሚገኙ የዞኑ ክፍሎች ላይ ለሚገኙ ማኅበረሰቦች ፈረስ ሁለ ነገራቸው ነው።

በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና ቅርስ አሥተዳደር መምህር እና የአለቃ ገብረሐና የባሕል ጥናት ዳይሬክተር መምህር መሠረት ወርቁ ለደቡብ ጎንደር አካባቢ ማኅበረሰብ ፈረስ ማረሻው፣ የደስታ ጊዜ ማጀቢያው፣ በሀዘን ጊዜም መሸኛው ነው ይላሉ።

ኢትዮጵያ ከሌሎች የውጭ ሀገራት ጋር የተለያዩ ጦርነቶችን ስታደርግ የፈረስ ሚና ከፍተኛ ነበር ብለዋል። የፈረስ ባሕሪ ጦርነትን ለመመከት ምቹ ነውም ይላሉ መምህሩ።

ተሽከርካሪዎች ባልነበሩበት በዚያ ዘመን የተሽከርካሪዎቹን ሚና ይወጣ ነበር ብለዋል። ፈረስ ታዛዥ ነው፤ በቀላሉ ለመገራት የሚመች ነው። ፈረስ ስንቅ እና ትጥቅ በማቀበልም ባለውለታ የነበር ዛሬም ባለውለታ እየኾነ ያለ እንስሳት ነው ብለዋል።

በአጠቃላይ ፈረስን ለሃይማኖታዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎት ማዋል በደቡብ ጎንደር እና አካባቢው የተለመደ ነው።

ፈረስ በደብረ ታቦር እና አካባቢው የክብር መገለጫ ነው፤ አሁን ሰው ምን ያህል ሃብት አለው? እንደሚባለው ሁሉ ምን ዓይነት ፈረስ አለው? የጭነት፣ የመጓጓዣ፣ የሽምጥ ተብሎ ይጠየቅ እንደነበር የታሪክ መምህሩ ተናግረዋል።

ለመጋለብ እና ለጉግስ አገልግሎት የሚውሉ ፈረሶች በልዩ እንክብካቤ የሚያድጉ ናቸው። በቀደም ጊዜ ፈረስ ለማርባት በደቡብ ጎንደር እና አካባቢው ራሱን የቻለ ሜዳ ይዘጋጅ ነበር፤ እስቴ አምቦ ሜዳ ደግሞ የባዝራ ፈረሶች ይረቡበት እንደነበር ታሪክ ይነግረናል ብለዋል የታሪክ መምህሩ።

ከጥንት ጀምሮ ፈረስ ማርባት እና መንከባከብ የሚያውቀው የደብረ ታቦር እና አካባቢው ሰው የፈረስ ጉግስ ውድድር የሚያደርግበት የራሱ የኾነ ጊዜ እንደ ነበረውም ታሪክ ያስረዳል።

በወቅቱ የአካባቢው ገዥዎች መሳፍንቱ እና መኳንንቱም ይሳተፉ እንደ ነበር በፈረንጆቹ አቆጣጠር 1837 ወደ ኢትዮጵያ የመጣው አርኖ ሚሸል ዳባዲ በፈረንሳይኛ ቋንቋ የጻፈው እና ገነት አየለ አንበሴ የተረጎመችው በኢትዮጰያ ከፍተኛ ተራሮች ቆይታዬ ክፍል አንድ መፅሐፍ ገጽ 143 ላይ በገና ጨዋታ ማግስት ወደ ማታ ላይ ራስ ዓሊ የፈረስ ጉግስ ሊጫወቱ ይመጣሉ ስለተባለ በዛው ሔድን” ይልና ስለፈረስ ጉግሱ አጨዋወት ይገልጻል።

ራስ ዓሊ ፈረስ ላይ አቀማመጣቸው ያማረ ባይኾንም ጥሩ ይጋልባሉ ሲልም ጽሑፍ ያትታል።

መምህር መሰረት ደብረ ታቦር አጅባር ላይ ከገና በዓል ማግስት ባለው ወቅት ይከወን የነበረው የፈረስ ጉግስ ጨዋታ በአጼ ቴዎድሮስ ጊዜ ከተማዋ የሀገሪቱ ዋና ከተማ ከመኾኗ ጋር ተያይዞ ይበልጥ የደመቀ እንደነበርም ይነገራል ነው ያሉት። በኋላም በአጼ ዮሐንስ አራተኛ በአካባቢው የሰመርነሃን ቤተ መንግሥት መገንባታቸው እና ከተማዋን በቋሚነትም ባይኾን በንጉስ ከተማነት ይጠቀሙባት ስለነበር የአጅባር የፈረስ ጉግስ የደመቀ እንደነበር ያስረዳሉ።

አጅባር ላይ ይደረግ የነበረው የፈረስ ጉግስ ጨዋታ ለመዝናኛነት ታስቦ የሚደረግ ብቻ አይደለም ይላሉ መምህር መሰረት ይልቁንም የጦር ልምምድ ማድረጊያ እንደ ነበር ያነሳሉ። አጅባር ላይ የፈረስ ጉግስ ሲከወን ጥሩ ጉግስ ተጫዋች ከኾነ በወታደርነት ይመለመል እንደነበርም ታሪኩን አጣቅሰው ገልጸዋል።

ይህ ልዩ የኾነው የደብረ ታቦር የፈረስ ጉግስ በአጼ ምኒልክ ዘመን እየተቀዛቀዘ መጥቷል። ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት ይላሉ የታሪክ ምሁሩ የሀገሪቱ የመንግሥት መቀመጫ ወደ መሀል ሀገር ወይም አዲስ አበባ መዘዋወሩ እንደነበር ይጠቅሳሉ።

በኋላ ግን በአካባቢው የራስ ጉግሳ ወሌ መሾም የአካባቢውን የፖለቲካ እንቅስቃሴ ብቻ ሳይኾን የፈረስ ጉግሱንም ከመፋዘዝ አነቃቃው ብለዋል።

የቅዱስ መርቆርዮስ ጽላት ያለበትን መንበረ መንግሥት ልጅቱ ማርያምን ራስ ጉግሳ ካደሱ በኋላ የቅዱስ መርቆርዮስ ታቦት ጥር 25 1940 ዓ.ም አካባቢ አጅባር ወርዶ እንዲከበር ትዕዛዝ ሰጡ ይላል ታሪኩ።

የደብረ ታቦር የፈረስ ጉግስም በወርሐ ጥር መጀመሪያ ሳምንት ይደረግ የነበረው ወደ ጥር 25 ተዘዋወረ ብለዋል።

ይህ ዘመን ያስቆጠረ የፈረስ ጉግስ ጨዋታ በአሁኑ ሰዓት ሁሌም ወርሐ ጥር በመጣ ቁጥር በጉጉት የሚናፈቅ ነው። የአካባቢውን ባሕል፣ እምነት እና ልማድ እያሳየ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደመቀ እና እያማረ መምጣቱን የታሪክ ባለሙያው አስረድተዋል።

አሁን ላይ የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር እና ደብረ ታቦር ዩኒቨርስቲ ከቤተክርስቲያኒቱ ጋር በመኾን የማልማት እና የማስተዋወቅ ሥራ በመሥራታቸው አዲስ የቱሪዝም መዳረሻ እንዲኾን አስችሎታል ነው ያሉት። ለቀጣይም ይህን ተግባር የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባም አንስተዋል።

የቅዱስ መርቆርዮስ የንግስ እና የጉግስ በዓል ባማረ እና በደመቁ መልኩ በደብረ ታቦር ከተማ አጅባር ሜዳ እና በእስቴ አምቦ ሜዳ እየተከበረ ይገኛል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሰማዕታቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ቅዱስ መርቆርዮስ ከፈረስ ጋር ምን አገናኛቸው?
Next article“ከቀደመ ባሕላችን ጋር አስተሳስረን፣ከታሪካችን ጋር አዋሕደን፣ ከዘመኑ ጸጋዎቻችን ጋር አሰናስለን ልንጠቀምበት ይገባል” አቶ መልካሙ ፀጋዬ