
ባሕር ዳር: ጥር 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖት እና ትውፊት መሠረት መላዕክትን፣ ጻድቃንን፣ ሰማዕታትን፣ ነቢያትን፣ ደናግላን እና መነኮሳት ሁሉም ለእግዚአብሔር ፍጹም አምላክ፣ ፈጣሪነት ሩኅሩህ አባትነት ታምነው እና ለኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ሲሉ ላደረጉት ተጋድሎ እና ለከፈሉት መስዋዕትነት መታሰቢያ ቀናት ተለይተው በዓላት ይከበሩላቸዋል።
በስማቸው ታቦተ ሕግ ተቀርጾ፣ ቤተ ክርስቲያን ታንጾ እግዚአብሔር ይቀደስ ይወደስባቸዋል፣ ምዕምናን ይጸልዩ ይዘክሩባቸዋል፣ በጾም በጸሎትም ይማጸኑባቸዋል።
ቅዱሳኑ የሚዘከሩባቸው በዓላት በታላቅ ድምቀት ይከበራሉ። በበዓላቱም ታቦታት ከመንበራቸው ወጥተው በካህናት እና ዲያቆናት ጸሎት፣ ቅዳሴ እና ውዳሴ፣ ወረብ እና ሽብሻቦ፣ በምዕመናን እልልታ እና ሆታ ታጅበው ወደ ማደሪያቸው ወርደው ወይም በአጸዳቸው ዞረው ተመልሰው ወደ መንበራቸው ይገባሉ።
የቅዱስ መርቆርዮስ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ በዓላት ብዙ ጊዜ በፈረስ ግልቢያ እና ትርኢቶች ታጅበው ይከበራሉ።
ለመኾኑ የሰማዕታቱ ቅዱስ መርቆርዮስ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ታሪክ ከሌሎቹ በምን ይለያል? ሰማዕታቱን እና ዓመታዊ የመታሰቢያ በዓላቸውን ከፈረስ ጋር ምን አገናኘው?
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የደብረ ዓባይ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የመጽሐፍ ትርጓሜ እና የቅኔ መምህር ሐረገወይን በሪሁን አብዛኞቹ ሰማዕታት ወታደሮች የነበሩ፣ ጀግና ተዋጊዎች እና ብዙ ተጋድሎ ያደረጉ ናቸው ይላሉ። ሰማዕታት ስለ ክርስቶስ ሕመም እና ሞት፣ ስለ እግዚአብሔር አንድነት እና ሦስትነት፣ ሃይማኖት ለሰው ልጆች ስላለው ሥጋዊ እና መንፈሳዊ፣ ምድራዊ እና ሰማያዊ ጥቅም፣ ስለሃይማኖታቸው የመሰከሩ እና ዋጋ የከፈሉ ናቸው።
ዘመኑም በ276 ዓ.ም አካባቢ፣ ዲዮቅልጥያኖስ የተባለው ንጉሥ በነገሠበት ዘመን፣ የመከራ ዘመን ወይም ዘመነ ሰማዕታት ተብሎ በተሰየመው 40 ዘመን ጊዜ ነበር ይላሉ።
ሰማዕታቱም ለእግዚአብሔር በመታመናቸው የተፈጸመባቸው ግፍ ከሌላው የተለየ እና የበለጠ በመኾኑ ያንን ጊዜ ዘመነ ሰማዕታት ተባለ።
ሰማዕት ማለት ቁሞ መከራ የተቀበለ ማለት ነው። እንደነ ጊዮርጊስ እና መርቆርዮስ መፈጨት፣ መቆላት፣ ገደል ውስጥ መጣል ነው ይላሉ። ሰማዕታት እንደማንኛውም ሰው ኾነው ተፈጥረው የነገሥታት እና የባለጸጎች ልጆች እና ወታደሮች ነበሩ። ነገር ለእግዚአብሔር ፍቅር መከራን የተቀበሉ፣ በሃይማኖት የጸኑ ናቸው።
ከሰማዕታት ውስጥ ዋናው ቅዱስ ጊዮርጊስ የሹም ልጅ ሲኾን አባቱ ሲሞት ሹመት ለመውረስ ለአርባ ዓመታት ክርስቲያኖችን ዋጋ ወዳስከፈለው ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ ለመቅረብ ተነሳ። በዚያ ወቅት ሀገሬው በሙሉ ክርስቲያን ነኝ የሚል አልነበረም።
ከመንገድ ላይ ያገኙት ሰዎችም በዚያ ሀገር ክርስቲያን ነኝ የሚል ሰው ሁሉ እንደሚገደል ነግረው የለበሰውን ልብስ፣ ክርስቲያንነቱን የሚያመላክቱ ነገሮቹን እንዲተው እና ወደ ንጉሡ እንዳይቀርብ መከሩት። እርሱ ግን ባለመፍራት በሃይማኖቴ ምክንያት ምድራዊ እና ስጋዊ ክብር አላስቀድምም አለ። ይዞት የነበረውን እጅ መንሻ ትቶ፣ አጃቢዎቹን መልሶ፣ ገንዘቡን በትኖ በነጭ ፈረሱ ወደ ንጉሡ ዲዮቅልጥያኖስ ሄዶ ክርስቲያንነቱን እና በክርስቶስ አማኝነቱን ነግሮ የሃይማኖት ምስክርነቱን ሰጠ ይላሉ መምህሩ።
ንጉሡም ጊዮርጊስን በሹመት እና በማዕረግ ለመሸንገል ሞከረ። ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን ይህ ሁሉ ሹመት ከሃይማኖቴ በታች ነው አለው። አንተ የምታመልካቸው ጣዖታት እስትንፋስ የላቸውም። የኔ አምላክ ግን ሁላችንም የፈጠረ ሕይወት ያለው እና ሕይወትን የሚሰጥ ነው። ሹመት፣ ሽልማት እና ሀብቱ ይቅርብኝ አለ ነው የሚሉት መምህሩ።
በዚህም ምክንያት ለሰባት ዓመታት ታስሮ፣ ሲገረፍ እና ሲሰቃይ ኖሮ በ27 ዓመቱ ሚያዝያ 23 ቀን በሰይፍ አንገቱ ተቀልቶ ተሰውቷል ይላሉ።
በእናት እና አባቱ ቤት እንደማንኛውም ወጣት ስጋዊ፣ መንፈሳዊ፣ ወታደራዊ ትምህርት ሲማር ያደገው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሥነ ምግባር ታንጾ አድጎ በሰባት ዓመታት ስቃዩ ለሦስት ጊዜ ስጋው ተፈጭቶ እስከመበተን ቢደርስም በእምነት ጽናቱ እና በእግዚአብሔር ኃይል መልሶ እየተነሳ ተጋድሎ ያደረገ ሰማዕት ነው። ፈረሰኛ ነውና ፈረሰኛው ጊዮርጊስ እየተባለ ይጠራል።
ቅዱስ መርቆርዮስም ሮማዊ ሲኾን የወታደር ልጅ ወታደር ነው። ቅዱስ መርቆርዮስ በገባበት የጦር ሜዳ ሁሉ የማይሸነፍ፣ ኃያል እና ጀብደኛ ወታደር እንደነበረ ይነገራል።
ዳኬዎስ በሚባለው የዘመኑ ንጉሥም አባቱ አገልጋይ ወታደር ነበሩ።የቅዱስ መርቆርዮስ የስሙ ትርጓሜ ገብረ ኢየሱስ የክርስቶስ አገልጋይ ማለት ነው ይላሉ መምህሩ።
ባለግርማ ሞገሱ ወታደር መርቆርዮስ በአንድ ወቅት ከውጊያ ሲመለስ ንጉሡ ክርስቶስን እንደካደ ሰማ። ከድሉ ማግስት ስጦታ እና ገንዘብ ከንጉሡ ቢላክለትም አልቀበልም አለ። ወደ ንጉሡ እንዲቀርብ በተደጋጋሚ ቢላክበትም ባለመቅረቡ አስገዳጅ ወታደሮች ተላኩበት። የተላኩት ወታደሮች ፈርተውት የነበረ ቢኾንም መርቆርዮስ ግን በጸጋ እግዚአብሔር አስቀድሞ ስለተገለጠለት የጦር ትጥቁንም ሁሉንም ነገር ጥሎ፣ ባዶ እጁን፣ በትህትና ተቀበላቸው።
ንጉሡ እንደሚፈልጉት እና አለባበሱን እንዲያሳምር ሲነግሩትም ባለመስማማት በመናኛ አለባበስ ወደ ንጉሡ ቀረበ። ንጉሡም በመርቆርዮስ ድል ደስ በመሰኘቱ የበለጠ እንደሚሾመው ነገረው። መርቆርዮስ ግን አንተ ስለካድከው ስለክርስቶስ ብየ ሹመቱን ተውኩት ብሎ ለንጉሡ መለሰ። ፍቅር ሁልጊዜ ኀይለኞችን ደካማ ባለጸጎችን ድሃ ያደርጋል እና ከአሁን በኋላ እኔ የክርስቶስ ወታደር ነኝ ብሎም መለሰ።
ንጉሡም አስገርፎ፣ በብረት አልጋ ላይ አስተኝቶ በእሳት እያነደደ እንዲቃጠል አዘዘበት። መርቆርዮስም ከብዙ ስቃይ አንገቱን ተቆርጦ በመስዋዕትነት አረፈ ይላሉ። እርሱም ፈረሰኛ ነውና በእርሱ በዓል ጊዜ ፈረስ ይታወሳል።
ቤተክርስቲያንም የእነዚህን ሰማዕታት በዓል ስታከብር በመንፈሳዊ ተጋድሏቸውም ኾነ በፊት የነበሩበትን የወታደርነት እና ፈረሰኝነታቸውን አብራ እንደምትዘክር መምህሩ ይናገራሉ። ኢትዮጵያውያንም ለወታደርነት ባላቸው ክብር እና ከፈረሰኝነት ጋር ባላቸው ከፍተኛ እና የቆየ ቁርኝት ምክንያት የእነዚህን ሰማዕታት በዓል ሲዘክሩ በከፍተኛ የፈረስ ሰልፍ፣ ውድድር እና ትርኢት አድርገውት እንደቀጠሉ ነው የሚናገሩት።
ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ፈረሰኞቹን በፈረስ ያጅቧቸዋል። በፈረስ ክብር ይሰጧቸዋል። በፈረስ ላይ ኾነው ያመሰግኗቸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!