
ደብረ ታቦር: ጥር 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ታቦር ከተማ በየዓመቱ ጥር 25 ቀን የሚከበረው የቅዱስ መርቆሬዎስ በዓል ዘንድሮም በድምቀት ማክበር ተጀምሯል።
በዋዜማው የተለያዩ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ክዋኔዎች ተፈጽመዋል። ሊቃውንት እና ካህናት ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ሲያስኬዱ የከተማ አሥተዳደሩ የከተማዋን ገጽታ ውበት የሚገልጹ እና ለዓለም የሚያሳውቁ ባሕላዊ እና ልማታዊ ክዋኔዎችን ከከተማዋ እና አካባቢው ነዋሪዎች ጋር እየፈጸመ ነው።
የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ኃይለኢየሱስ ሰለሞን በዓሉን አስመልክተው ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን መግለጫ ሰጥተዋል።
እንኳን ለቅዱስ መርቆሬዎስ የንግሥ እና የፈረስ ጉግስ በዓል አደረሳችሁ ያሉት አቶ ኃይለኢየሱስ በደብረ ታቦር ከተማ በድምቀት የሚከበረውን የቅዱስ መርቆሬዎስ በዓል ለማክበር ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል።
የቅዱስ መርቆሬዎስ የንግሥ እና የፈረስ ጉግስ በዓል ለተከታታይ ዓመታት በድምቀት ሲከበር ቆይቷል። በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ጭምር ሥራዎች እየተሠሩ ነውም ብለዋል።
በዓሉን ደማቅ፣ ጎብኝዎችን የሚስብ እና ምቹ ለማድረግ ሰፊ ሥራ ስንሠራ ቆይተናል። በዚህም ታሪካዊቷ አጅባር የምትደምቅበት እና ደብረ ታቦር የምትሞሸርበት የደስታ እና የምስጋና ቀን ይኾናል።
የመርቆሬዎስ በዓል እና የፈረስ ጉግስ ክዋኔው ረጅም ታሪክ ያለው እንደኾነ የጠቀሱት አቶ ኃይለኢየሱስ በ1840ዎቹ ከእነ ራስ ዓሊ ጀምሮ በኋላም በእነ ራስ ጉግሳ ጭምር ሲከበር እንደነበር አስታውሰዋል።
ደብረ ታቦር የተለያዩ ነገሥታት መቀመጫ የነበረች ከመኾኗ ጋር ተያይዞ ነገሥታት የፈረስ ጉግስን አጅባር ሜዳ እና ደብረ ታቦር ኢየሱስ ካለው ሜዳ ላይ ሲያስደርጉ እንደነበር ታሪክ ይነግረናል ብለዋል። እናም ፈረስ ጉግስ እና ደብረ ታቦር የተቆራኘ እና የቆየ ታሪክ አላቸው ብለዋል።
ይህንን ደማቅ በዓል የዓለም ቅርስ ለማድረግ ጭምር እየተሠራ እንደኾነም አቶ ኃይለ ኢየሱስ ገልጸዋል የመርቆሬዎስ በዓል ቀደምት ነገሥታት ያከብሩት የነበረው ከመኾኑ ጋር በተያያዘ ለደብረ ታቦር ከተማ ልዩ ትርጉም አለው። ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና የቱሪዝም መስህብ እንዲኾንም እየሠራን ነው ብለዋል።
ደብረ ታቦር ከተማ እና አካባቢዋ በተፈጥሮ የታደለች እና በታሪክ የከበረች በመኾኗ ይህንን ሀብት የበለጠ ማልማት እንዳለብን አስበን የቱሪዝም ሀብታችንን ለማልማት የበለጠ እንሠራለን።
ከተማ አሥተዳደሯ በአራቱም ማዕዘን መንገዶች፣ አስተማማኝ መብራት፣ ተስማሚ አየር፣ ጥሬ ሃብት እና ለኢንቨስትመንት ምቾት ያላት በመኾኗ ሠርቶ የሚታደርባት እና የሚታደግባት መኾኗን ገልጸዋል። ይህንን እድል በማስፋት የበለጠ እንድትለማ እና እንድትጠቀም እንደሚደረግም ገልጸዋል።
ከተማ አሥተዳደሩም ልማት ናፋቂ በመኾኑ አልሚ ባለሀብቶችን በቀናነት ለማስተናገድ የመሬት፣ የመሠረተ ልማት እና ሌሎች ምቹ ኹኔታዎችን ፈጥረን ባለሀብቶችን እየጠበቀ ነው ብለዋል።
ደብረ ታቦር ላይ መጥተው ቢያለሙ ተጠቃሚ ስለሚኾኑ ወደ ከተማችን መጥተው እንዲያለሙ ለባለሀብቶችን ጥሪያችንን እናስተላልፋለን ብለዋል አቶ ኃይለኢየሱስ።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!