” ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ የአደባባይ በዓላት ከቱሪዝም ሀብትነታቸው በተጨማሪ የሕዝባችን አንድነት ማሳያዎች ናቸው” አቶ ይርጋ ሲሳይ

33

ባሕር ዳር: ጥር 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ ለቅዱስ መርቆርዮስ ዓመታዊ ክብረ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ የአደባባይ በዓላት ከቱሪዝም ሀብትነታቸው በተጨማሪ የሕዝባችን አንድነት ማሳያዎች ናቸው ነው ያሉት።

በጥንታዊቷ ደብረ ታቦር ከተማ እና በእስቴ መካነ ኢየሱስ በባሕላዊ የፈረስ ጉግስ ልዩ ትዕይንት ታጅቦ የሚከበረው የቅዱስ መርቆርዮስ በዓለ ንግሥ አንዱ የባሕላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶቻችን ጥምረት የፈጠረው ውብ የሕዝባችን ገጽታ ነው ብለዋል።

የቅዱስ መርቆርዮስ በዓለ ንግሥ በደብረታቦር እና እስቴ ዴንሳ በልዩ ሁኔታ የሚከበር መኾኑን ያነሱት ኀላፊው የአካባቢውን ማኅበረሰብ ባሕላዊ፣ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ እና ሃይማኖታዊ ቀደምት እሴቶችን ለቱሪዝም ገበያ በማዋል የሀገር ውስጥ ቱሪዝሙን ለማሳደግ ይጠቅማል ነው ያሉት። ከቱሪዝም ጥቅሙ ባሻገር ውስጣዊ ኅብረትን በማስፋት የሕዝባችንን አንድነት ለማሳደግ የሚጠቅም ነው ብለዋል።

እንዲህ አይነት ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ እሴት ያላቸውን በዓላት የቱሪስት መስህብ ማዕከል እንዲሆኑ ማድረግ በሚያስችል ሁኔታ ማክበራችን ከስድስት ምዕተ ዓመት በላይ የቆየችው ታሪካዊቷ ደብረ ታቦርም ሆነ የታላቁ ንጉሥ የአፄ ፋሲለደስ የልጅነቱ መቦረቂያና የእናቱ ንግሥት ወልደ ሳህላ መናገሻ፤ የሊቃውንቱ መፍለቂያ የሆነችው እስቴና አካባቢያቸው የቱሪዝም ምጣኔ ሃብት ተቋዳሽና የቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችን ሕያው አሻራዎች እንዲተዋወቁ ማድረጊያ አቅሞቻችን ናቸው ነው ያሉት በመልክዕታቸው።

የቅዱስ መርቆሪዎስ በዓል ጥር 25 በየዓመቱ በልዩ የፈረስ ጉግሥ ትርኢት እና ሌሎች ዝግጅቶች ታጅቦ እንደሚከበርም አንስተዋል። ሃይማኖታዊ ገጽታውንም ኾነ ባሕላዊ እሴቱን በጠበቀ መንገድ በማክበር የሕዝባችን የባሕልና ቱሪዝም ሃብቶች ማስተዋወቅ ከሁላችንም የሚጠበቅ ዐቢይ ጉዳይ ነው ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ለቅዱስ መርቆርዮስ ዓመታዊ ክብረ በዓል እንኳን አደረሳችሁ” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next articleየብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ በሦስተኛ ቀን ውሎው የፓርቲውን ፕሬዚደንትና ምክትል ፕሬዚዳንቶች ምርጫ በማካሄድ ላይ ነው።