
ደብረ ማርቆስ: ጥር 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ማርቆስ ከተማ የነዳጅ አቅርቦት እና ስርጭት ላይ በተደጋጋሚ ቅሬታዎች ሲነሱ ይስተዋላል፡፡ በነዳጅ እጥረት ምክንያት ረጃጅም የተሸከርካሪ ሰልፎችን በየማደያዎቹ መመልከት የተለመደ ተግባር ከኾነ ሰነባብቷል፡፡
በነዳጅ አቅርቦት እና ስርጭት ጉዳይ ከኅብረተሰቡ በተደጋጋሚ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ የሰጡት የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ዮሴፍ መለሰ ችግሩ በስፋት የሚስተዋል መኾኑን አረጋግጠዋል፡፡
ነዳጅ ከጅቡቲ ተጓጉዞ ወደ ተጠቃሚው እስኪደርስ ድረስ የሚፈጠር መጓተት፣ የአቅርቦት እና ፍላጎት አለመጣጣም፣ ሕገ ወጥ የነዳጅ ግብይቶች መበራከት እና የቁጥጥር መላላት በየጊዜው ለሚታየው ችግር ምክንያቶች መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ዮሴፍ ማብራሪያ ነዳጅን በሕገ ወጥ መንገድ ሲያዘዋውሩ እና ሲሸጡ በተገኙ አካላት ላይ በተወሰደው ርምጃ ከ5 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል፡፡ ኀላፊው በበጀት ዓመቱ ለከተማዋ ይቀርባል ተብሎ ከታቀደው በላይ ነዳጅ ወደ ከተማው መግባቱን ተናግረዋል።
በዚህም ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሊትር በላይ ናፍጣ እና ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሊትር በላይ ቤንዚን ለተጠቃሚዎች መቅረቡን ነው የተናገሩት፡፡
ያም ኾኖ የፍላጎት መጨመር እና የሕገ ወጥ ተግባራት መበራከት በተለይ በቤንዚን በአቅርቦት ላይ እጥረት እንዲከሰት አድርጓል ነው ያሉት፡፡ በከተማዋ ከ10 በላይ ማደያዎች ቢኖሩም ነዳጅን ፍትሐዊ በኾነ መልኩ ከማሰራጨት አኳያ ክፍተቶች መኖራቸውን የተናገሩት ኀላፊው ነዳጅን በአግባቡ እና በወቅቱ ለተጠቃሚው ለማሰራጨት የኩፖን ሥርዓትን ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ስለሺ ተመሥገን በክልሉ ያጋጠመው የጸጥታ ችግር፣ የሕገ ወጥ ታክሲዎች ቁጥር መበራከት እና ዘርፉን በአግባቡ መቆጣጠር አለመቻሉ የነዳጅ አቅርቦት እና ስርጭት ላይ ቅሬታዎች እንዲነሱ ምክንያት ኾኗል ብለዋል፡፡
ምክትል ከንቲባው በጅቡቲ ወደብ ላይ የሚስተዋለውን መስተጓጎል ለመቅረፍ ከክልሉ ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ጋር በመነጋገር ችግሩን ለማቃለል እየተሠራ ነው ብለዋል።
ቅንጅታዊ አሠራርን ተግባራዊ በማድረግ ከነዳጅ አቅርቦት እና ስርጭት ጋር የተያያዙ ሕገ ወጥ ድርጊቶችን ለመከላከል እና ፍትሐዊ የነዳጅ ስርጭትን ለማረጋገጥ እየተሠራ ስለመኾኑም አመላክተዋል፡፡
አሽከርካሪዎች፣ የተሸከርካሪ ባለቤቶች እና ኅብረተሰቡ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተባባሪ በመኾን ሕገ ወጥ የነዳጅ ዝውውር እና ግብይትን የመከላከል ኀላፊነቱን እንዲወጣም ተጠይቋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!