በአማራ ክልል በሌማት ትሩፋት ትልቅ ለውጥ እየታየ መኾኑ ተገለጸ።

38

ባሕር ዳር: ጥር 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት የ2017 በጀት ዓመት የሥድስት ወራት የሥራ አፈጻጸሙን ገምግሟል። በግምገማው የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጋሻው ሙጬ (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

የግመገማው ተሳታፊዎች በእንስሳት ሃብት ልማት ላይ ትልቅ ጥቅም እየተገኘ መኾኑን ገልጸዋል። በየአካባቢው የእንስሳት ሃብት አጠቃቀም እና ልማት ለውጥ እያሳየ መኾኑን አንስተዋል። ነገር ግን የእንስሳት ሃብት ማቀነባበሪያ፣ የእንስሳት መኖ አቅርቦት፣ የእንስሳት ተዋጽኦን የሚያቆዩ ቴክኖሎጂዎች እጥረት በሚፈለገው ልክ ውጤት እንዳይገኝ አድርጓል ነው ያሉት።

ክልሉ ካለው የእንስሳት ሃብት ልማት አንጻር በተገቢው መንገድ እንዲጠቀም አሠራሮችን ማስተካከል፣ በጥናት እና ምርምር የተደገፈ የእንስሳት ሃብት ልማት ሥራ መሥራት ይጠበቃል ብለዋል። አዲስ እና የተሻሻለ የመኖ ዘር ማቅረብ፣ እንስሳትን ማዳቀል እና ዝርያቸውን ማሻሻል ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በአማራ ክልል ምክር ቤት የግብርና፣ አካባቢ ጥበቃ እና ውኃ ሃብት ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ከፍያለው ሙላቴ በአማራ ክልል በሌማት ትሩፋት ብዙ ስኬቶች እና ውጤቶች እየተገኙ ነው ብለዋል። በከተሞች ላይ ሰፋፊ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል።

ከሕዝብ ፍላጎት አኳያ ብዙ የሚቀሩ ሥራዎች ቢኖሩም የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት እየሠራቸው ያሉ ሥራዎች ትምህርት ሊሰጡ የሚችሉ መኾናቸውን ነው የተናገሩት። እየተሠሩ ያሉ የሌማት ትሩፋት ሥራዎች የኑሮ ውድነቱ እንዳይባባስ እያገዙ ነውም ብለዋል። ሥራዎቹ የበለጠ እየተስፋፉ ከሄዱ ትልቅ ለውጥ ይመጣል ነው ያሉት። ተቋማት በሌማት ትሩፋት ሥራ በመሳተፍ ራሳቸውን መቻል እንደሚገባቸውም አመላክተዋል።

የእንስሳት ምርቶችን በተገቢው መንገድ ማቀነባበር እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። ባለሀብቶችም በዚህ ዘርፍ መሳተፍ አለባቸው ብለዋል። ምክር ቤቱ ሥራዎችን እየተከታተለ ችግሮች እንዲፈቱ፣ ጥንካሬዎች እንዲቀጥሉ እንደሚያደርግ ነው የተናገሩት። የእንሰሳት ሃብት ጥራትን መጨመር እና ምርታማነትን ማሳደግ ይጠበቅብናል ብለዋል። ዝርያ ካልተሻሻለ የተሻለ ዕድገት እንደማይገኝም አመላክተዋል።

የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጋሻው ሙጬ (ዶ.ር) የአማራ ክልል በእንስሳት ሃብት እምቅ አቅም እንዳለው ገልጸዋል። የእንስሳት ሃብት ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱንም ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲዎች በእንስሳት ሃብት ልማት መሳተፍ እንደሚጠበቅባቸውም ገልጸዋል። በእንስሳት ሃብት ልማት ማኅበራት እየተደራጁ የተሻለ ሥራ እየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል። በዓሣ ሃብት ልማትም ወጣቶች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲኾኑ ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል። በክልሉ ሰፊ የኾነ የማር ምርት መኖሩን የተናገሩት ኀላፊው ወጣቶች በማር ምርት የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲኾኑ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት። የማር ምርት ለውጭ ገበያ እየቀረበ መኾኑንም አንስተዋል።

በክልሉ ያሉ የመኖ አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት እየተሠራ መኾኑን የተናገሩት ኀላፊው በክልሉ የመኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች እየተበራከቱ መኾናቸውን ተናግረዋል። የመኖ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ ይሠራል ነው ያሉት። የሰው ኃይልን በማቀናጀት የኅብረተሰብን ፍላጎት መሠረት ያደረጉ ሥራዎች ይሠራሉ ነው ያሉት።

የእንስሳት ሃብት ልማት ምርቶች ጊዜ የሚሰጡ አይደሉም ያሉት ኀላፊው ምርቶቹ እንዳይበላሹ ለማድረግ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን ማስፋፋት ያስፈልጋል ብለዋል። በክልሉ መቀንጨርን ለመከላከል የእንስሳት ተዋጽኦን በሚገባ መጠቀም ይገባል ነው ያሉት። የእንሳሳት ሃብት ምርቶች በአግባቡ ለማኅበረሰቡ እንዲደርሱ ከንግድ እና ገበያ ልማት ጋር እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል።

በሌማት ትሩፋት እንቅስቃሴ ጥሩ ውጤት መገኘቱንም ገልጸዋል። በሌማት ትሩፋት በከተሞች ብቻ ለእንስሳት ሀብት ልማት ለሼድ ግንባታ የሚኾን ከ522 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ጠቁመዋል። ይህም ከዚህ በፊት ያልነበረ እና አዲስ እሳቤ ነው ብለዋል። ከተሞች የእንስሳት ሃብት ልማት ቦታ መለየታቸውንም ተናግረዋል። ይህ እንደ ክልል ትልቅ ለውጥ ነው ብለዋል።

ምርት ቀጥታ ከተጠቃሚው ጋር እንዲገናኝ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። አሚኮ የእንስሳት ሃብት ልማት ትኩረት እንዲያገኝ እና እንዲሠፋ እያደረገ ላለው ሥራም አመስግነዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleታጥቀው በጫካ የሚንቀሳቀሱ አካላት ወደ ሰላም በመመለስ የልማቱ አጋዥ እንዲኾኑ የተሀድሶ ሥልጣኞች ጠየቁ።
Next article456 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ተመለሱ።