
ባሕር ዳር: ጥር 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት የ2017 በጀት ዓመት የሥድስት ወራት የሥራ አፈጻጸሙን እየገመገመ ነው። በግምገማው የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጋሻው ሙጬ (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢዎችን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።
በአማራ ክልል ከፍተኛ የኾነ የእንስሳት ሃብት እንዳለ ይነገራል። ክልሉ ለእንስሳት ሃብት ልማት የተመቸ እንደኾነ ተገልጿል። የአማራ ክልል በእንስሳት እና በዓሣ ሃብት ልማት እንደ ሀገር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተመላክቷል። በክልሉም ከፍተኛ የኾነ የምጣኔ ሃብት ድርሻ ያለው መኾኑ ነው የተገለጸው።
በግምገማው ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጋሻው ሙጬ (ዶ.ር) የክልሉ የምጣኔ ሃብት የጀርባ አጥንት ግብርና ነው፤ ለግብርና ደግሞ የጀርባ አጥንቱ እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ነው ብለዋል።
እንስሳት ሃብት ልማት ለሥርዓተ ምግብ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለውጭ ምንዛሬ፣ ለአጠቃላይ የምጣኔ ሃብት ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውም ነው ያብራሩት። እንስሳት ሃብት ልማት ከማኅበረሰብ አኗኗር ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው መኾኑንም አንስተዋል። የእንስሳት ሃብት ምርት እና ምርታማነትን በመጨመር የኅብረተሰብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በ2017 በጀት ዓመት ያለውን እምቅ ሃብት መሠረት ያደረገ ዕቅድ በማቀድ መሥራታቸውን ገልጸዋል። ጥንካሬዎችን የበለጠ በማጠናከር ድክመቶችን ደግሞ በማሻሻል መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት። ክልሉ ሰፊ እና ያልተነካ ሃብት አለው ያሉት ኀላፊው የእንስሳት ሃብት ምርት እና ምርታማነትን በመጨመር የኅብረተሰብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይጠበቅብናል ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!