“በጉባኤው ዛሬን እና ነገን የሚያስተሳስሩ የቀጣይ አቅጣጫዎችን እናስቀምጣለን” አቶ አደም ፋራህ

51

ባሕር ዳር: ጥር 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ ጉባዔ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል። በጉባኤው የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ በተጨባጭ እምርታዊ ጉዞ ከአያሌ ስኬቶች እና ድሎች ማግስት “ከቃል እስከ ባሕል” በሚል መሪ መልዕክት ለምናደርገው ጉባኤ እንኳን በደህና መጣችሁ ብለዋል።

ከተለያዩ ሀገራት ወዳጅነትን በማስቀደም በጉባኤው ላይ ለመታደም የመጡ የእህት ፓርቲ መሪዎችን አመሥግነዋል። ብልጽግና ፓርቲ ሚዛናዊነትን እና አሥተሳሳሪ ትርክትን መሠረት በማድረግ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የነበሩ ተቃርኖዎችን የሚያሳታርቅ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ ዓላማ ይዞ የተቋቋመ ፓርቲ መኾኑንም አንስተዋል። የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ሁሉንም ኢትዮጵያውያንን ያሳተፈ ዕውነተኛ ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲ ነው ብለዋል። ብልጽግና የሁሉንም ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ እየሠራ መኾኑን ነው የተናገሩት።

ቃልን በተግባር የማረጋገጥ ባሕላችን መሠረት አድርገን የገጠሙን ተግዳሮቶች ሕዝቡን በማሳተፍ በብቃት ተሻግረን፣ ከዕዳ ወደ ምንዳ ለመሻገር ጥንካሬ እና ጉድለታችን በልኩ እየለዬን፣ ወረቶችን እያስቀጠልን፣ የጎደለውን እየሞላን እና ፈተናን ወደ ዕድል እየቀየርን ለዛሬ እና ለነገ ትውልድ መብት ጥብቅና ቆመን፣ በሕልም ጉልበት ለእምርታዊ ዕድገት ተግተን ዛሬ ላይ ደርሰናል ነው ያሉት።

በሁለተኛው ጉባኤ በመጀመሪያው ጉባኤ ለሕዝብ ቃል የተገቡ የአፈጻጸም ደረጃቸውን በመፈተሽ የሕዝብ እርካታ እና በሀገራችን ዘላቂ ጥቅሞችን በመመዘን፣ የአመራር እና የአባላቱን ሁኔታ በጥልቀት በመገምገም ፓርቲው ቁመናችንን እንመረምራለን ብለዋል። በጉባኤው ዛሬን እና ነገን የሚያስተሳስሩ ቀጣይ አቅጣጫዎችን እናስቀምጣለን ነው ያሉት። ያለፉት ዓመታት ቃል በገቡት ልክ መተግበራቸውንም ገልጸዋል።

በስንዴ ምርት ራስን ከመቻል አልፈን ወደ ውጭ የላክንበት፣ በአረንጓዴ አሻራ ግንባር ቀደም ኾነን ክብር የተጎናጸፍንበት፣ ምርት እና ምርታማነትን በከፍተኛ ሁኔታ ያሳደግንበት፣ የሕዳሴ ግድብን የመገባደድ ደረጃ ላይ ያደረስንበት፣ ዘመናዊ የቱሪዝም መዳራሻዎችን በማልማት እና የቀደሙትን በማደስ የቱሪዝም ዘርፉን ያነቃቃንበት፣ ዲጂታል ኢትዮጵያን መሠረት በማድረግ ተቋማት ዘመኑን እንዲዋጁ ያደረግንበት፣ የማዕድን ሃብትን የጨመርንበት፣ ከተሞቻችን ለነዋሪዎቹ ምቹ እንዲኾኑ ያደረግንበት፣ በርካታ ሰው ተኮር ሥራዎችን፣ የኑሮ ውድነት ቅነሳ የሠራንበት፣ የተወረወሩብንን ቀስቶች በብልሃት አምክነን የሀገራችን ሉዓላዊነት ያስከበርንበት ዓመታት ናቸው ብለዋል።

ከስኬቶቹ በተጓዳኝ የፖለቲካ፣ የጸጥታ፣ የኢኮኖሚ እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮች ገጥመውናል ነው ያሉት። የተመዘገቡትን ውጤቶች ዘላቂነት ለማረጋገጥ እና ያጋጠሙንን ችግሮች ለማለፍ የውስጥ ፓርቲ ጥራትን ለማረጋገጥ ሰፋፊ ውይይቶችን እና ሥልጠናዎችን ማካሄዳቸውንም ገልጸዋል።

አመራር እና አባላትን ማጥራታቸውንም ተናግረዋል። በጉባኤው በጥልቀት እና በብስለት በመምከር ሁለንተናዊ ብልጽግናን የማረጋገጥ ጥረታችን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያደርሱ፣ የፓርቲውን የአመራር እና የአባላት ጥራት የሚያጠናክሩ አቅጣጫዎች እና ውሳኔዎች ይወሰናሉ ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ደም መቃባቱ ይብቃ በሚል ያለፈውን በመተው ወደ እርቅ መጥተናል” የጎሳ መሪዎች
Next articleየብልፅግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉበዔ ዛሬም ቀጥሎ ይካሄዳል።