
ተማሪዋ በተፈናቃዮች መጠለያ ውስጥ ሆናም ለፈተና ዝግጅት ላይ ናት።
በማዕከላዊ ጎንደር ብቻ ከ51 ሺህ በላይ ተማሪዎች ተፈናቅለዋል፤ በተያዘው መርሀ-ግብር መሠረት ክልላዊና ሀገር አቀፍ ፈተናዎችን ለመውሰድም ስጋት አለባቸው፡፡
ባሕር ዳር፡የካቲት 17/2011 ዓ.ም(አብመድ) በምዕራብ እና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች በተፈጠረው አለመረጋጋት በርካቶች ተፈናቅለዋል፡፡ በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳውሃ ከተማ፣ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ደንቢያ ወረዳ እና በላይ አርማጭሆ ወረዳ ትክል ድንጋይ አካባቢ በሚገኙ ጊዜያዊ የመጠለያ ጣቢያዎች ብዙዎቹ ተፈናቃዮች ተጠልለው ይገኛሉ፡፡

በአዘዞ በኩል ወደ ሱዳን የሚወስደውን መንገድ ተከትሎ የከተመች ትንሽ ከተማ ናት፤ አይንባ፡፡ በአይምባ ከተማ ሰሜናዊ በር በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ሜዳ ላይ ሰፍረዋል። አብዛኛው ሴቶች እና ሕጻናት ናቸው። የሚያጠቡ እናቶችን ትካዜ፣ ወተት አውርድ እያሉ የእናቶቿቸውን ጡት የሚጎትቱ ሕጻናትን አሳዛኝ ትዕይንት ተመለከትሁ።
በመጠለያው የሚገኙትን አንዳንዶቹን ጠየኳቸው፤ አብዛኛዎቹ ከአደዛ፣ አንከር፣ አውራረዳ፣ ቀን ወጣ፣ ብሆና እና ላዛ ቀበሌዎች የመጡ ናቸው። የቅርብ ወገኖቻቸውን በተፈጠረው ግጭት አጥተዋል፡፡ አርሶ አደሮች፣ እናቶችና እና እንቦቀቅላ ሕጻናት፣ ባለ ምርኩዝ አዛውንቶች …ከሞቀ ቤታቸው ወጥተዋል ፤ ለስቃይ ተጋልጠዋል።
ተፈናቃዮችን እየተመለከትሁ እያለሁ የአንዲት ታዳጊ ድርጊት ቀልቤን ሳበው። እንደ ሜዳ በተዘረጋው የተፈናቃዮች መንደር፣ ዋይታ በበዛበት የብሶት ገበያ ቀይ ብዕር ከወረቀት ጋር አገናኝታ የምትሞነጫጭር ልጅ ላይ ዓይኔ አረፈ።

በድርጊቷ ባለችበት ስቃይ ውስጥም የነገ ተስፋን ማለም እንደሚቻል አሳየችኝ። ታዳጊዋ ቅድስት ሰለሞን ትባላለች፤ ተፈናቃይ የ8ኛ ክፍል ተማሪ ናት። በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጭልጋ ወረዳ ላዛ ቀበሌ ትኖር ነበር። አሁን ከቀየዋም ከትምህርት ገበታዋም ተፈናቅላ በጊዜያዊ የመጠለያ ቦታ ትኛለች፡፡
ግጭቱ የቤተሰቦቿን ቤት በእሳት እንዲወድም አድርጓል። የቀለም ቤቷ የላዛ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም ሙሉ በሙሉ በእሳት ሲጋይ በዓይኗ ማየቷን እንባ እያቀረረች ነግረኛለች። ትምህርት ተቋርጧል፤ ተማሪዎች ተበትነዋል፤ አስተማሪዎቿም የሉም።
ትምህርት ቤቷ ተቃጥሎ ትምህርት ባይኖርም፣ የቀለም አባት አስተማሪዎቿ ከአካባቢው ቢሰወሩም ቅድስት በችግር ውስጥ ሆናም ልክ እንደሌሎች በምቹ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉ የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች የዘንድሮውን ክልል አቀፍ ፈተና ለመፈተን ከወዲሁ እየተዘጋጀች ነው።
ቅድስት ተስፋ ቢጠወልግም፣ ጨለማው ድቅድቅ ቢሆንም መንጋቱ የማይቀር መሆኑን የተረዳች የአብሪ ኮከብ ተምሳሌት ሆና ታየችኝ፡፡ በማዕከላዊ እና በምዕራብ ጎንደር ዞኖች ብልጭ፣ ድርግም የሚለው የአካባቢው ሰላም በርካታ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ተረጋግተው እንዳይከታተሉ እያደረገ መሆኑን ከአንደበታቸው ሰምተናል፤ ተመልክተናልም፡፡

አብመድ ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ያገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በተፈጠረው ችግር ምክንያት በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ብቻ 107 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና 5 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፡፡
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን እርካቤ እንደተናገሩት በአጠቃላይ በዞኑ 51ሺህ 18 ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ከተፈናቃይ ተማሪዎች መካከል 4ሺህ 15 የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና ተፈታኞች ናቸው፡፡ በቅርቡ በሚሰጠው ሀገር አቀፍ ፈተና መፈተን የነበረባቸው 2ሺህ 602 የ10ኛ እና 1ሺህ 488 የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችም ትምህርታቸውን አቋርጠዋል፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሙላው አበበ በበኩላቸው ‹‹በአማራ ክልል ምዕራብ እና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖችን እንዲሁም ራያ አካባቢዎች በግጭት ምክንያት ከተምህርት ገበታ ውጭ የሆኑ የክልሉ ተማሪዎች 51ሺህ 94 ናቸው፤ 5ሺህ 482 የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች፣ ቀሪዎቹ 45ሺህ 612ቱ ደግሞ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች ናቸው›› ብለዋል፡፡ ከተፈናቃይ ተማሪዎች መካከል 10ሺህ 401 የሚሆኑት በጊዜያዊ የመጠለያ ጣቢያዎች ሆነው ሰላም ሰፍኖ ትምህርታቸውን ለመከታተል የሚጠባበቁ ናቸው፡፡
አብመድ ከኢፌዴሪ የትምህርት ሚኒስቴር ያገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በተለያዩ ምክንያቶች በተፈጠሩ ችግሮች 1ሺህ 200 የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አገልግሎት መስጠት አቁመዋል፡፡ አብዛኞቹ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እና በሶማሌ ክልሎች የሚገኙ መሆናቸው ነው የተነገረው፡፡
ዋናው ነገር ግጭት በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች ሰላም ሰፍኖ እነዚህ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሀገር ተረካቢ ታዳጊ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንደቀደሙ ተረጋግተው እንዲማሩ ማድረግ ነው እና መንግሥት ምን እየሠራ ነው? በዘንድሮው የሀገር አቀፍም ይሁን ክልል አቀፍ ፈተና ተማሪዎቹ ተሳታፊ ይሆናሉ ወይስ አይሆኑም? የሚለውን ጥያቄ አብመድ አንስቷል፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙላው አበበ ትምህርት በተቋረጠባቸው ቦታዎች የሚገኙ ወላጆች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሚመለከታቸው ሁሉ ለአካባቢዎቹ ሰላም መሆን የበኩላቸውን ሚና ሊጫወቱ እንሚገባ አሳስበዋል፡፡ በተለይ ‹‹የክልል አቀፍም ይሁኑ የሀገር አቀፍ ፈተና መውሰድ ያለባቸው ተማሪዎች እንዲፈተኑ ከወዲሁ ጥረት እያደረግን ነው›› ብለዋል አቶ ሙላው፡፡ ‹‹ፈተናውን እንዴት እና መቼ መፈተን እንዳለባቸው ከተማሪዎች እና ከወላጆቻቸው ጋር ውይይት አድርገን የሚካካሱ የትምህርት ጊዜዎችን አካክሰን እንዲፈተኑ ለማድረግ ተወስኗል›› ነው ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፡፡
በኢፌዴሪ የትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ቤት ማሻሻል ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ወጋሳ በበኩላቸው ‹‹በዓመቱ መሰጠት ያለባቸው ክልል እና ሀገር አቀፍ ፈተናዎች በተያዘላቸው መርሀ ግብር የሚሰጡ ይሆናሉ፤ በግጭት ምክንያት ትምህርታቸውን መከታተል ያልቻሉ ተማሪዎች ትርፍ ጊዜያቸውን ተጠቅመው በማካካሻ መማር ያለባቸውን ትምህርት እንዲማሩ ለማድረግ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል›› ነው ያሉት፡፡
ነገር ግን የ8ኛ፣ የ10ኛ እና የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና መውሰድ ያለባቸው በችግር ውስጥ ያሉ ተማሪዎችን በተመለከተ ውይይት ተደርጎበት ወደፊት እልባት የሚያገኝ መሆኑን ነው የጠቆሙት፡፡
ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ