
ከሚሴ: ጥር 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር በደዌ ሀራዋ ወረዳ ለረጅም ጊዜያት በተለያዩ ምክንያቶች ግጭት ውስጥ የነበሩ ጎሳዎች በሀገር ሽማግሌዎች እርቅ አውርደዋል። አሚኮ ያነጋገራቸው እርቅ ያወረዱ የጎሳ መሪዎች እስከዛሬ አጥጋቢ ባልኾነ ምክንያት ደም ሲቃቡ እና ሲፈናቀሉ መቆየታቸውን ገልጸዋል። አሁን ግን ደም መቃባቱ ይብቃ በሚል ያለፈውን በመተው ወደ እርቅ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
ከዚህ በኋላም ያለፈውን በመተው አንድ ላይ ለአካባቢው ሰላም እና ልማት በጋራ እንደሚሠሩ ገልጸዋል። እርቅ እንዲወርድ ለደከሙ አካላትም ምሥጋና አቅርበዋል። የደዌ ሀራ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ መሐመድ ሷብር ሀጂ በሁለቱ ጎሳዎች መካከል የነበረውን ግጭት ሕዝቡ በሚያምንበት በሀገር ሽማግሌ በኩል ማስታረቅ መቻሉን አንስተዋል።
የተፈጠረው ሰላም የወረዳው ኗሪ ለሰላም፣ ለእርቅ እና ለልማት እንደሚቆም ያሳየበት መኾኑን የተናገሩት አሥተዳደሪው ከዚህ በኋላ ወረዳው ትልቅ የልማት ቀጣና ኾኖ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር የሰላም ካውንስል ጸሐፊ አሕመድ ጁሀር የሰላም ካውንስሉ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሰላም እና ጸጥታ ኀላፊዎች፣ ከወረዳ እና ዞን መሪዎች ጋር በጋራ በመሥራቱ እርቅ ወርዶ ሰላም ሊመጣ እንደቻለ ገልጸዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክትል አሥተዳዳሪ እና የሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ አብዱ ጀማል በሁለቱ ጎሳዎች ምክንያት ወረዳውም ኾነ ብሔረሰብ አሥተዳደሩ ችግር ውስጥ ኾኖ መቆየቱን አብራርተዋል።
ሁለቱን ጎሳዎች ከረጅም ጊዜ ጥረት በኋላ በባሕሉ መሠረት ማስታረቅ መቻሉንም ተናግረዋል።የሁለቱ ጎሳዎች መታረቅ ለወረዳው፣ ለብሔረሰብ አሥተዳደሩ እና ለአጎራባች ወረዳዎች ሰላም የማይተካ ሚና እንዳለውም ጠቅሰዋል።
ምክትል አሥተዳዳሪው በአካባቢው ሰላም መስፈኑ ካሁን በኋላ ሙሉ አቅማችንን ወደ ልማት ለማዞር ይረዳናል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ መስዑድ ጀማል
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
