
ሁመራ: ጥር 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በዘላቂ ልማት እና ሰላም ግንባታ ላይ የሴቶች ሚና ከፍተኛ መኾኑን የሰቲት ሁመራ ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ጽሕፈት ቤት ገልጿል። ጽሕፈት ቤቱ “የሴቶች የተደራጀ ሁለንተናዊ አበርክቶ ለዘላቂ ሰላም እና ልማት ግንባታ” በሚል መሪ መልዕክት የሴቶች የውይይት መድረክ በከተማ አሥተዳደሩ አካሂዷል።
በልማት እና በሰላም ጉዳዮች ላይ የሴቶች አስተዋጽኦ ጉልህ መኾኑን የከተማ አሥተዳደሩ ብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ገነት ፍታለው አስረድተዋል። ሴቶች የጸጥታ መዋቅሩን በቻሉት አቅም እየደገፉ እና እያገዙ መኾኑንም ኀላፊዋ ተናግረዋል። በተለያዩ ኬላዎች ላይ ፍተሻ እና ጥበቃ ከማድረግ ጀምሮ ለጸጥታ መዋቅሩ ስንቅ በማዘጋጀት እና በማቅረብ የሴቶች አጋርነት የጎላ መኾኑንም ጠቅሰዋል።
ኀላፊዋ ሴቶች ከሰላም ግንባታ ባሻገር በከተማ ግብርና በመሠማራት በኢኮኖሚው ዘርፍም የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት እየሠሩ ናቸው ብለዋል። በብድር እና ቁጠባ በመደራጀት፣ በመስኖ ሥራ እና በዶሮ እርባታም በመሠማራት የተሻለ እንቅስቃሴ እያደረጉ መኾኑንም ጠቅሰዋል። በመድረኩ የተሳተፉት ወይዘሮ ጥበበ መኮነን “የሀገርን ሰላም ለማስጠበቅ እና ኢኮኖሚዋን ከፍ ለማድረግ የሴቶች አቅም አይተኬ ነው” ብለዋል።
ለዚህች ሀገር ግጭት አይጠቅምም ያሉት ወይዘሮ ጥበበ በየትኛውም ጎራ ያሉ ወገኖች እንዳይጎዱ የሴቶች ሚና ከፍተኛ መኾኑንም ገልጸዋል።
ሰላምን ለማረጋገጥ እና ልማትን ለማፋጠን የሴቶች ንቁ ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ የገለጹት ሌላኛዋ የመድረኩ ተሳታፊ ወይዘሮ መሠረት ዋሴ ናቸው።
በዞኑ በተለያዩ ከተሞች የውይይት መድረኩ እንደሚቀጥል ከዞኑ የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የሴቶች ሊግ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
