
ባሕር ዳር: ጥር 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ጎጃም ዞን ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ የስድስት ወር የሥራ አፈጻጸም የግምገማ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ አካሂዷል። የሰሜን ጎጃም ዞን ፖሊስ መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ያለምዛፍ ጥላሁን በዞኑ በነበረው የጸጥታ ችግር ከፍተኛ ቀውስ ገጥሞ ነበር ብለዋል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ የጸጥያ ኀይል በጋር በመኾን በሠራው ሥራ አንጻራዊ ሰለም ማምጣት ተችሏል ነው ያሉት። ተዘግተው የነበሩ ተቋማት ወደ መደበኛ ሥራቸው እንደተመለሱም ገልጸዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት የዞኑ ፖሊስ፣ ሚሊሻ፣ ሰላም አስከባሪ፣ አድማ መከላከል ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር በመኾን ጸረ ሰላሞች ላይ እርምጃ በመውሰድ፣ ሰርጎ ገብን አድኖ በመያዝ እና ሌሎች የጸጥታ ማስከበር ተግባር ላይ በጽናት በመታገል ለውጥ መገኘቱ ተናግረዋል። ሠራዊቱ ሰላምን ለማጽናት ወደፊትም የተጠናከረ ሥራ ያከናውናል ነው ያሉት።
የሰሜን ጎጃም ዞን ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ገብረሥላሴ ታዘብ በዞኑ አሁን ላይ የሕግ የበላይነት እየተረጋገጠ እና ሰላም እየሰፈነ ነው ብለዋል። ማኀበረሰቡን በማደራጀትም የወንጀል መከላከል ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል ነው ያሉት። በውይይት ሰላምን ማስፈን ወሳኝነት አለው ብለዋል። “በውይይት ጫካ ገብተው የነበሩ በርካታ ታጣቂዎች የሰላምን መንገድ እንዲከተሉ ማድረግ ተችሏል” ነው ያሉት።
በአንዳንድ አካባቢዎች ኀብረተሰቡ በግልጽ ጸረ ሰላም ኃይሉን እየተቃወመ ነው ያሉት ኀላፊው ሰላምን ባልመረጡት ላይ እርምጃ በመውሰድም ሰላሙን እያረጋገጠ መኾኑን ነው ያነሱት። በግምገማው የተገኙ ተሳታፊዎች መንግሥታዊ አደረጃጀቱን በማጠናከር እና ኀበረተሰቡን አወያይቶ ከመንግሥት ጎን በማሰለፍ የአካባቢውን ሰላም መጠበቅ ተችሏል ብለዋል።
አሁን ላይ የተሻለ ሰላም መኖሩንም ገልጸዋል። የጸጥታ መዋቅሩም ይበልጥ ተጠናክሮ ሰላምን እያጸና እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የጸጥታ ኃይሉ 24 ሰዓት በሚያደርገው ጥበቃ አሁን አንጻራዊ ሰላም ሰፍኗል ብለዋል። የጸጥታ ኃይሉ እና ኀብረተሰቡ በቅንጅት በመሥራታቸው የተሻለ ሰላም እንደተገኘ ተናግረዋል። በጸጥታ ችግር ተፈናቅለው የነበሩትም አሁን የተሻለ ሰላም በመስፈኑ ወደ ቀያቸው ተመልሰው መደበኛ ሥራቸውን ጀምረዋል ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
