ኅብረተሰቡን በማሳተፍ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በትኩረት እየተሠራ ነው።

53

ደሴ: ጥር 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ወሎ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ የስድስት ወራት አፈፃፀሙን የሁሉም ወረዳ እና ከተማ አሥተዳደር የሰላምና ጸጥታ ኀላፊዎች በተገኙበት እየገመገመ ነው። የከላላ ከተማ አሥተዳደር ሰላምና ፀጥታ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስር አለቃ ጀማል ሙህዬ ከኅብረተሰቡ ጋር ተከታታይ ውይይት በማድረግ በርካታ ወገኖች የሕዝብን እና የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው በሰላማዊ መንገድ መቀላቀላቸውን ተናግረዋል።

የቦረና ወረዳ ሰላምና ፀጥታ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሃምሳ አለቃ ቃሲም ዳኜ አሁን የተገኘውን ሰላም በማጽናት የመልካም አሥተዳደር እና የልማት ሥራዎች በተሳካ ኹኔታ እንዲቀጥሉ የሚያስችል እቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል። የደቡብ ወሎ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ረዳት ኮሚሽነር ዘለቀ አለባቸው በየደረጃው የጸጥታ መዋቅሩ ኅብረተሰቡን በማሳተፍ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

የጸጥታ ችግሩን በመፍታት በዞኑ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች በአግባቡ እንዲተገበሩ ምቹ ኹኔታ መፍጠር ተችሏልም ነው ያሉት፡፡ የሰላም ጥሪውን የተቀበሉ በርካታ ታጣቂዎች የተሐድሶ ሥልጠና እየወሰዱ ወደ ኅብረተሰቡ ከመቀላቀል ባለፈ ወደ ጸጥታ መዋቅሩ እየገቡ በሰላም እና በልማት እየተሳተፉ ነው ብለዋል ረዳት ኮሚሽነሩ፡፡

አሁን ያለውን ሰላም በማጽናት ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የጸጥታ መዋቅሩ ኅብረተሰቡን አሳትፎ በትኩረት ይሠራልም ብለዋል፡፡

የሰላምን አማራጭ በማይቀበሉት ላይ የሕግ ማስከበር ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ረዳት ኮሚሽነሩ ኅብረተሰቡ አንድነቱን ጠብቆ ሰላሙን ለማጽናት ከመንግሥት እና ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር የጀመረውን ትብብር ማጠናከር ይኖርበታል ነው ያሉት፡፡

ዘጋቢ ፦አንተነህ ፀጋዬ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበማዕከላዊ ጎንደር ዞን አንጻራዊ ሰላም መምጣቱን የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ገለጸ።
Next article“በውይይት ጫካ ገብተው የነበሩ በርካታ ታጣቂዎች የሰላምን መንገድ እንዲከተሉ ማድረግ ተችሏል”የሰሜን ጎጃም ዞን ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ