በማዕከላዊ ጎንደር ዞን አንጻራዊ ሰላም መምጣቱን የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ገለጸ።

55

ጎንደር: ጥር 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር እና የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የስድስት ወር የሕግ ማስከበር አፈጻጸም እና የቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ውይይት በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ነው። በውይይቱ ከጎንደር ከተማ እና ማዕከላዊ ጎንደር ዞን የተውጣጡ የጸጥታ አካላት ተገኝተዋል።

በክልሉ ተከስቶ የነበረው የሰላም እጦት ዜጎች በሰላም ወጥተው እንዳይገቡ አድርጎ መቆየቱን የተናገሩት የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ በሪሁን መንግሥቱ መከላከያ ሠራዊቱ እና የክልሉ የጸጥታ መዋቅር በቅንጅት በሠሩት ሕግ የማስከበር ሥራ አንጻራዊ ሰላም መምጣቱን ገልጸዋል።

ሕግ የማስከበር ሥራው በተገቢው መንገድ መከናወኑ ወደ ልማት እንድንገባ አስችሏል ያሉት ምክትል ኀላፊው ለዚህ ማሳያውም የጎንደር ከተማ ልማት ነው ብለዋል። በሌላ በኩልም በጎንደር ከተማ በድምቀት የተከበረው የጥምቀት በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር መከበሩ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።

ሰላምን የመረጡ ታጣቂ ኀይሎችን ወደ ሕዝቡ የመቀላቀል ሥራም የሚቀጥል መኾኑን አቶ በሪሁን ገልጸዋል። በጎንደር ከተማ አሥተዳደር የሰላም እጦቱ እገታ እና ዘረፋ የመሳሰሉ ወንጀሎች እንዲፈጸሙ ምክንያት ኾኗል ያሉት የከተማ አሥተዳደሩ ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ አለልኝ ዓለም ይህንን የወንጀል ድርጊት ለመከላከል ከማኅበረሰቡ ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች ተደርጓል ብለዋል።

በሌላ በኩል የጸጥታ መዋቅሩን በማጠናከር በኩልም ሰፊ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል። በተሠራው የሕዝብ ግንኙነት እና የጸጥታ መዋቅር ማደራጀት ተግባራት ሕዝቡ እፎይታ እንዲያገኝ ማስቻሉን አቶ አለልኝ ገልጸዋል። ቀጣይነት ያለው ሰላም ለማምጣትም ማኅበረሰቡን የማወያየት እና የጸጥታ መዋቅሩን የማደራጀት ሥራ እንደሚሠራም ገልጸዋል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን በበኩሉ ባለፉት ስድስት ወራት የዞኑን ሰላም ለመመለስ ሕዝባዊ የማወያየት እና የጸጥታ መዋቅሩን የማደራጀት ሥራ መሠራቱን የዞኑ ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ አንተነህ ታደሰ ገልጸዋል። በዚህም ጥያቄ አለን ብለው ወደ ጫካ የገቡ ኀይሎችን የመመለስ እና አንጻራዊ ሰላም ማምጣት መቻሉን ገልጸዋል።

በቀጣይነትም ጥያቄ ያላቸው አካላት ጥያቄያቸውን በማቅረብ ወደ ውይይት እንዲመጡ የማድረግ ሥራ ይሠራል ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ ጉባዔ እየተካሄደ ነው።
Next articleኅብረተሰቡን በማሳተፍ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በትኩረት እየተሠራ ነው።