በደብረ ታቦርና ወረታ ከተሞች በሦስት ቀናት ብቻ 671 ዩኒት ደም ተሰብስቧል፡፡

928

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 25/2012 ዓ.ም (አብመድ) የደቡብ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ ሙላት አሻግሬ ደም ለጋሽ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች አለመኖር እና የተደራጀ እንቅስቃሴ አለመኖር በዞኑ የደም እጥረት ተከስቶ ነበር ብለዋል፡፡

በዞኑ ባሉ ዘጠኝ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ሰጭ የሕክምና ተቋማት የደም እጥረት በመፈጠሩ ታካሚዎች ሪፈር እየተባሉ መቆየታቸውን አቶ ሙላት ለአብመድ ተናግረዋል፡፡

ኃላፊው እጥረቱን ለመፍታት የሥራ ኃላፊዎች እና በጎ ፍቃደኞች ባደረጉት የተደራጀ ርብርብ ባለፉት ሦስት ቀናት ብቻ 671 ዩኒት ደም ከደብረ ታቦርና ወረታ ከተሞች ብቻ መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

‘‘የደም አሰባሰብ ሂደቱ ከታቀደው አንጻር በእጥፍ እየሄደ ነው’’ ያሉት አቶ ሙላት በቀጣይም ከ16 የወረዳ ዋና ዋና ማዕከላት ላይ የማሰባሰብ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

በደም አሰባሰብ ሥራው የደብረ ታቦርና ወረታ ከተማ አስዳደር ነዋሪዎችና የዙሪያዎቹ አርሶ አደሮች ያሳዩትን ተሳትፎና የልግስና ተግባር ‘‘በደም እጥረት ሪፈር የሚባሉ ዜጎችን ሕይወት የሚታደግና የሚያስመሠግን ተግባር ነው’’ ብለዋል፡፡

በአንድ ሳምንት አንድ ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ እቅድ እንዳላቸው የተናገሩት አቶ ሙላት በተደራጀው የደም አሰባስብ ቡድን በየሦስት ወራቱ ተመሳሳይ ሥራ ለማስቀጠል ማቀዳቸውንም ተናግረዋል፡፡ የዞኑ የደም ባንክ የዕቅድ አፈጻጸም ከዓመታዊ ዕቅዱ አንጻር 80 ከመቶ መድረሱንም አስታውቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ

Previous articleሱዳን ባለፉት 24 ሰዓታት 59 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውን በምርመራ አረጋገጠች፡፡
Next articleበኩር ሚያዚያ 26/2012