
ባሕር ዳር: ጥር 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 85ኛው የአገው ፈረሰኞች በዓል “አርበኝነታችን ለአሁናዊ ሰላማችን” በሚል መሪ መልዕክት በእንጅባራ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው። በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ሚኒስትር ዴዔታ ተስፋሁን ጎበዛይ ጀግኖች አባቶቻችን እና እናቶቻችን ኢትዮጵያን ቀኝ ለመግዛት የመጣውን ቅኝ ገዢ አሳፍረው በመመለስ የመንፈስ ብርታት አውርሰውናል ብለዋል።
ለሀገር መስዋዕትነት የከፈሉ ፈረሶችን እና ፈረሰኞችን ለመዘከር የአገው ፈረሰኞች በዓል በየዓመቱ እንደሚዘከር ገልጸዋል። የአገው ፈረሰኞች በዓል የተከፈለው መስዋዕትነት እና የጀግንነት ዋጋ በትውልዱ እንዲታሰብ የሚያደርግ መኾኑን ነው የተናገሩት።
ፈረስ ከአገው ሕዝብ ጋር የጠበቀ ግንኝነት እንደላውም ገልጸዋል። የአገው ሕዝብ የሀገሩን ክብር፣ አንድነት እና ማኅበራዊ ማንነቱን በሁለንተናዊ ጀግንነት አጽንቶ የኖረ ሕዝብ መኾኑንም ገልጸዋል። የአገው ፈረሰኞች በዓል የአገው ሕዝብ ለሀገሩ ክብር ዋጋ የከፈሉትን ሁሉ አክብሮ የሚያስከብር አስተዋሽ ሕዝብ መኾኑን ያሳያል ነው ያሉት።
የአገው ፈረሰኞች ከሌሎች ኢትዮጵያን ጋር ተባብረው የኢትዮጵያን ነጻነት እንዳስከበሩት ሁሉ እኛም የዚህ ዘመን ትውልዶች የአባቶቻችን መስዋዕትነት በማስታወስ የሚጠበቀውን የብሔራዊነት ግዳጅ ልንወጣ ይገባል ብለዋል።
በዓሉን በድምቀት ማክበር የቻልነው ሰላም በመስፈኑ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው የተሟላ ሰላም በአማራ ክልል እና በመላው ሀገራችን እንዲሰፍን መንግሥት ስላማዊ አማራጭን ከሚከተሉ ጋር ሰላማዊ አማራጭን ለመጠቀም በሩ ክፍት መኾኑን ነው የተናገሩት።
የሰላም አማራጭን ለሚመርጡ ወንድም እህቶቻችን በድጋሜ ጥሪ እናስተላልፋለን ነው ያሉት። ኢትዮጵያ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ፣ ታሪካዊ እና ባሕላዊ ኹነቶችን በዩኔስኮ ማስመዝገቧን ገልጸዋል። አሁን በዩኔስኮ እንዲመዘገቡ እየተሠሩ ካሉ ኹነቶች መካከል አንደኛው የአገው ፈረሰኞች በዓል ነውም ብለዋል።
በዓሉን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የተጀመሩ ተግባራት እንዲሚቀጥሉም ገልጸዋል። በዓሉ በድምቀት እየተከበረ እዚህ እንዲደርስ ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
