
ባሕር ዳር: ጥር 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 85ኛው የአገው ፈረሰኞች በዓል “አርበኝነታችን ለአሁናዊ ሰላማችን” በሚል መሪ መልዕክት በእንጅባራ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው።
በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳደሪ ቴዎድሮስ እንዳለው እንግዶቻችን እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋል። ኢትዮጵያ በጋራ ሕልም የተጋመዱ፣ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ምናባዊ እና ሥርዓታዊ ወቅር ፈጥረው የሚኖሩባት መስተጋብራዊት ሀገር ናት ብለዋል።
“ኢትዮጵያዊነት ብዝኃ ማንነት ነው” ያሉት አሥተዳዳሪው ብዝኃ ማንነታችን ደግሞ የጋራ ማንነታችን እና እኛነታችን ነው ብለዋል። እኛነታችን በትናንት፣ በዛሬ እና በነገ መስተጋብራችን የተጋራነው ነው፣ ኢትዮጵያ በጋራ ሕልም የሚገናኙ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የአብሮነት ውቅር ፈጥረው የሚኖሩባት ናት ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በውስን ማንነቶች ብቻ የተገነባች አለመኾኗንም አንስተዋል። የቀደምት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ብዝኀ ማንነት ያለባት ኅብረ ብሔራዊት ሀገር ናት ብለዋል።
ሕዝቦቿ ደግሞ የየራሳቸው ወግ እና ባሕል ያላቸው ኅብረ ብሔራዊ ናቸው ነው ያሉት። ሀገራችን የጋራችን ናት፣ በጋራ ገንብተናል ፣ በጋራ ጠብቀናል፣ በአርበኝነት እና በአብሮነት ተሰናስለን እዚህ ደርሰናል ብለዋል። በኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በኅብረ ብሔራዊነት ተጠብቃ የኖረች ሉዓላዊነት ሀገር መኾኗንም ገልጸዋል።ወራሪ ጠላት በእብሪት ተነስቶ ሀገራችንን ለመውረር ሲሞክር ጀግኖች በአንድነት ተነስተው ለሀገራችን ሉዓላዊነት ታላቅ ገድል ፈጽመዋል ነው ያሉት።
የአገው ሕዝብ በሀገራዊ ግንባታ ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ ያለው ባለ ደማቅ ታሪክ መኾኑን ገልጸዋል። የአገው ሕዝብ ለሀገር ያበረከተውን አስተዋጽኦ በጥር 23 እንደሚዘክረውም ተናግረዋል። የአገው ፈረሰኞች በዓል የፈረስ እና የፈረሰኞችን ውለታ የሚያከብር መኾኑን አንስተዋል። የአገው ሕዝብ እና ፈረስ ጥብቅ ግንኙነት አላቸው ያሉት አሥተዳዳሪው ፈረስ ለአገው ሕዝብ ያደርሳል፣ ያርሳል፣ ያዋጋል ነው ያሉት። ፈረስ የወግ ማዕረጉ አካል ነው ብለዋል። የአገው ሕዝብ ፈረስን የልብ አድርስ እያለ እንደሚያወድስም ገልጸዋል።
የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት የአርበኞቻችን እሴት መጠቀም ይገባል ነው ያሉት። የአገው ፈረሰኞች ድሮም ኾነ ዛሬ ለሰላም ይጥራሉ ብለዋል። ሰላም እንዲመጣ ይመክራሉ ይዘክራሉ ነው ያሉት።
ብዝኃ ማንነት ባሉባት ሀገር ብዝኃ ፍላጎቶች መኖራቸው አይቀሬ ነው ያሉት አሥተዳደሪው ብዝኃ ፍላጎት መኖራቸው የተሻሉ አማራጮች በመኾናቸው ለሁሉም የሚበጀውን አማራጭ መጠቀም ይገባል ብለዋል። በገዢው ሀሳብ መተማመን እና ልዩነትን በሰለጠነ መንገድ መፍታትን ከፈረሰኞች እሴት መማር ይገባል ነው ያሉት።
ፈረሰኞች በሰላማዊ መንገድ ችግሮችን መፍታትን ይመክራሉ ብለዋል። የአገው ሕዝብ ለስልጡን ሃሳብ ምንጭ መኾኑንም ገልጸዋል። የአገው ሕዝብ ታሪክ ቀደምት እና ሰፊ መኾኑንም ተናግረዋል። የአገው ሕዝብ ሰላማዊ አሥተዳደርን ያለማመደ ጥበበኛ መኾኑንም ገልጸዋል።
የአገው ፈረሰኞች በዓል በሀገር አቀፍ ደረጃ የማይዳሰስ ቅርስ ኾኖ መመዝገቡን አንስተዋል። በዓሉ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ መሥራት እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።
በጋራ የገነባናት አንዲት ሀገር አለችን ያሉት አሥተዳደሪው አንዳችን ለሌላችን ጥላ ከለላ ነን፣ እጣ ፋንታችንም የአንዳችን ጉዳይ የሁላችን ጉዳይ እንዲኾን ማስቻል ነው ብለዋል። ጽንፈኝነት ድንበር የሌለው የክፉ እሳቤዎች ውጤት መኾኑን አንስተዋል። ብዙዎች የራሳቸውን ፍላጎት ይዘው እየተነሱ ግጭት እየጠመቁ መኾናቸውን ነው የተናገሩት።
ጽንፈኝነትን በመታገል በኅብረ ብሔራዊነት የበለጸገች ሀገር መገንባት ይገባል ነው ያሉት። በአማራ ክልል ከአንድ ዓመት በላይ በዘለቀው ግጭት ሕዝባችን ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሏል ብለዋል። ይህ አደገኛ አካሄድ በቅርቡ ካልተቋጨ በስተቀር የክልላችን ሕዝብ የበለጠ አደጋ ይገጥመዋል ነው ያሉት።
የትኛውም ጽንፈኛ ኃይል አብሮነታችን አይበጥሰውም ብለዋል። በጫካ ውስጥ የሚገኙ ኃይሎች ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል። የሕዝብን ድምጽ እንዲሰሙም አሳስበዋል። ለአገው ሕዝብ ስነ ልቦና የማይመጥኑ እንወክልሃለን የሚሉ ኃይሎች መኖራቸውንም ገልጸዋል። የአገው ሕዝብ ከታላቅነት ለሚያወርደው ሃሳብ ጀሮ እንደማይሰጥም ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
