የአገው ፈረሰኞች በዓል የባሕል እሴቶችን ለትውልድ ለማስተላለፍ ጉልህ ሚና እየተወጣ ነው።

26

ባሕር ዳር: ጥር 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 85ኛው የአገው ፈረሰኞች በዓል በድምቀት እየተከበረ ነው። “አርበኝነታችን ለአሁናዊ ሰላማችን “በሚል መሪ መልዕክት እየተከበረ ባለው በዓል ላይ ፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች እና ሌሎች ታዳሚያን ተገኝተዋል።

በበዓሉ ላይ ንግግር ያደረጉት የእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ የኔዓለም ዋሴ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። በዓሉ የአገው ፈረሰኞች በዓል ይባል እንጂ ለመላ ኢትዮጵያውያን መታሰቢያ በዓል ስለመኾኑ ተናግረዋል።

የዚህ በዓል ዋና ዓላማ ከ120 ዓመታት በፊት በአድዋ ጦርነት እንዲኹም በጣሊያን ዳግም ወረራ ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን እና ፈረሶቻቸው የከፈሉትን መሥዋዕት እና ያሳዩትን ጀግንነት ለመዘከር ስለመኾኑ ነው የገለጹት።

የአገው ሕዝብ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ጉልህ ሚና እንደተወጣ እና እየተወጣ እንደሚገኝም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አውስተዋል።

የአገው ፈረሰኞች በዓል ሲከበር የባሕል እሴቶቻቸንን ለትውልድ ግንባታ እና ብልጽግና ከማስተዋወቅ ባሻገር ትውልዱ ከአባቶቻችን ስለአንድነት እንዲማር እና ለሀገር ግንባታ ህልም ያለው እንዲኾን ለማስቻል ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የበርካታ ቱባ ባሕል ባለቤት ስትኾን የአገው ፈረሰኞች ማኅበርም የዚሁ ማሳያ አንድ አካል መኾኑን የተናገሩት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ማኅበሩ 63 ሺህ አባል እንዳለው ገልጸዋል።

የዚህ ማኅበር አባላት በዓሉን ከማክበር በላይ አርቀው የሚያስቡ፣ የአባቶቻቸውን ሥራ የሚዘክሩ እና ምክራቸውንም የሚያከብሩ ስለመኾናቸውም ገልጸዋል።

አሁንም በእንጅባራ ከተማ እና አካባቢው ለተገኘው ሰላም የጸጥታ ኀይሉን አመስግነዋል።

ባለሀብቶች ወደ ከተማዋ መጥተው እንዲያለሙም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ጥሪ አስተላልፈዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleከተማ ውስጥ የነበሩ የጽንፈኛ ኀይል አባላት በቁጥጥር ውለዋል።
Next article“ኢትዮጵያዊነት ብዝኃ ማንነት ነው” አቶ ቴዎድሮስ እንዳለው