
ባሕር ዳር: ጥር 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “አርበኝነታችን ለአሁናዊ ሰላማችን” በሚል መሪ መልዕክት 85ኛው የአገው ፈረሰኞች በዓል እየተከበረ ነው። በበዓሉ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፍት የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጋርዳቸው ወርቁ (ዶ.ር) ዩኒቨርሲቲው የአገው ሕዝብን ባሕል እና የተፈጥሮ ጸጋ አውጥቶ በማስተዋወቅ ሰፊ ሥራ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው የአገውን ሕዝብ ቋንቋ እና ባሕል ብሎም የቱሪዝም ጸጋውን በማስተዋወቅ የሠራው ሥራ ከፍ ያለ መኾኑን አብራርተዋል። እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ከሀገሪቱ የልማት አቅጣጫ በመነሳት ቱሪዝም ላይ ትኩረት ሠጥቶ እየሠራ እንደኾነ ገልጸዋል። እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ በአካባቢው ያሉ የቱሪዝም ጸጋዎችን በማጥናት ለአጋር አካላት የማሳወቅ ተግባር እየተወጣ ነውም ብለዋል።
የአዊ ሀብት የኾኑትን የዘንገና እና የጥርባ ሐይቅን ጨምሮ ሌሎች የአካባቢው ሀብቶች በሀገራዊ ፕሮጀክቶች ታቅፈው ቢለሙ እና የግል ባለሀብቶችም ኾነ መንግሥት ቢያለማቸው ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው አካባቢ ስለመኾናቸው አብራርተዋል። በተለይም ዛሬ የሚከበረው የአገው ፈረሰኞች በዓል ከፍ ብሎ እንዲከበር ዩኒቨርሲቲው በሲምፖዚየም እና በሌሎችም ተግባሮች እየተሳተፈ ስለመኾኑ ነው ያብራሩት።
ዩኒቨርሲቲው የአገው ፈረሰኞች በዓል ለሀገር ያለውን ጠቀሜታ በመገንዘብ በዩኔስኮ በማይዳሰሱ ቅርሶች እንዲመዘገብ በማሰብ ጥናት አድርጎ ከክልል እስከ ፌዴራል ላሉ ተቋማት ሰነዱን ማስረከቡን ነው ያብራሩት።
የአገው ፈረሰኞች በዓል ሀገርን ከወራሪ ለማዳን የተከፈለን መስዋዕትነት መሠረት አድርጎ የተመሠረተ በመኾኑ ዝቅ ሲል የሀገሪቱ ከፍ ሲል ደግሞ የዓለም ቅርስ መኾን የሚገባው በመኾኑ ለዚህ ሁሉም አስፈላጊውን ጥረት እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!