
ፍኖተ ሰላም: ጥር 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎጃም ዞን በበጋ መስኖ ልማት፣ በአትክልት፣ ፍራፍሬ እና በስንዴ ልማት በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። የምዕራብ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ ተስፋዬ አስማረ በዞኑ 30 ሺህ 231 ሄክታር መሬት በተለያዩ ምርቶች ለማልማት ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
የበጋ መስኖ ሥራውን ለማከናወን 29 ሺህ 465 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እና 20 ሺህ 955 ኩንታል የምርጥ ዘር ግብዓት ስርጭት ተደርጓል ነው ያሉት። እየተከናወነ ባለው የበጋ መስኖ ልማት ላይም 3 ሚሊዮን 400 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
የፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መንገሻ እንኳሆነ በከተማ አሥተዳደሩ የሞተር ፓምፕ ስርጭት ተደርጓል ብለዋል። ከ1ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶአደሮች በማሰራጨት 599 ሄክታር መሬት በተለያዩ ምርቶች በበጋ መስኖ ልማት መሸፈኑንም ገልጸዋል።
በከተማ አሥተዳደሩ ከበጋ መስኖ በተጨማሪ የምርጥ ዘር ብዜት ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮችን የመደገፍ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል። የጃቢ ጠህናን ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስቻለ ሞሴ በወረዳው ለበጋ መስኖ ልማት የሚያስፈልጉ የውኃ ፓምፕ፣ የአፈር ማዳበሪያ እና የዘር ስርጭት በሚፈለገው ልክ መሰራጨቱን ተናግረዋል። 3 ሺህ 743 ሄከታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ታቅዶ እየተሠራ መኾኑንም አብራርተዋል።
በፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር በበጋ መስኖ ልማት በአትክልት፣ ፍራፍሬ እና በስንዴ ልማት የተሠማሩ አርሶ አደሮች ውጤታማ መኾናቸውን ተናግረዋል ።
በተለያዩ ምርቶች የዘር ብዜት ላይም ተሰማርተው እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል። ለዚህ ደግሞ በመንግሥት በኩል አስፈላጊው ነገር እየተደረገላቸው መኾኑን አርሶ አደሮች ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!