
ባሕር ዳር: ጥር 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል የሥነ-ምግባር እና ጸረ-ሙስና ኮምሽንን የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን ገምግሟል፡፡ የፌዴራል ሥነ-ምግባር እና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን በቴክኖሎጂ በመታገዝ እና አሠራሮችን በማዘመን የጸረ ሙስና ትግሉን ማጠናከር እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
አሠራሮችን ዲጂታላይዝድ በማድረግ ሙስናን ለመግታት የሚያስችል ስለኾነ የተጀመሩ በቴክኖሎጂ የታገዙ ሥራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል እና ሙስና የሚጠፋበትን ዘመናዊ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ቋሚ ኮሚቴው አመላክቷል፡፡ የሙስና ወንጀል የተወሳሰበ በመኾኑ በተደራጀ እና በቴክኖሎጂ በታገዘ መልኩ ለመቅረፍ እና ምንጩን ለማድረቅ በተለይ ባለፉት ስድስት ወራት የሀብት ምዝገባ ችግሮችን የሚፈታ ሥራ ተሠርቷል ተብሏል። የሕግ ማዕቀፎች እና ስታንዳርዶች ሲዘጋጁ እንደነበርም ተገልጿል።
የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቱ አለነ የሙስና ችግር በበርካታ ዘርፎች ውስጥ ተሰግስጎ የሚገኝ በመኾኑ በየዘርፎቹ ከፍሎ እና በቴክኖሎጂ ታግዞ መሥራት እና ችግሩን ማከም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የተቋማት መሪዎች እና የሥራ ኀላፊዎች ሙስናን ለመዋጋት በቁርጠኝነት መነሳሳት እና መሥራት እንደሚጠበቅባቸው የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አዝመራ አንዴሞ ገልጸዋል። እንደ ሀገር በርብርብ እና በቅንጅት በመሥራት የጸረ-ሙስና ትግሉን በማስቀጠል ሙስናን ማስወገድ እንደሚቻል እና ለዚህም በከፍተኛ ቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
መመሪያዎች፣ ሕጎች እና ደንቦችን ተከትሎ በመሥራት የተጠያቂነት መንፈስን በማጉላት መተግበር እንደሚገባም ተናግረዋል። ተቋማዊ የአሥተዳደር ሁኔታ መሠረታዊ ችግር ስለሆነ ሰፊ ሥራ መሥራት እና ተደራሽ ማድረግ የሚያስፈልግ ሲሆን ጥሩ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ተቋማት እንዲመሰገኑ ጥሩ ያልሠሩት ደግሞ እንዲወቀሱ ማድረግ እንደሚገባ የቋሚ ኮሚቴው አባላት አንስተዋል፡፡
የፌዴራል የሥነ-ምግባር እና የጸረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርቃቶ (ዶ.ር) የሙስና ወንጀልን ለመግታት ሁሉም ዜጋ ተረባርቦ እንዲንቀሳቀስ የሚያስችል ሥራ ሢሠራ እንደነበረ አስታውሰዋል። ሙስናን በመከላከል ረገድ የትውልድ ግንባታ እና የሀገር ግንባታ በመኾኑ ትውልድ ላይ እየተሠራ ባለው ሥራም የሚበረታታ ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።
ከክልል ጀምሮ ማስረጃ ላይ የተመረኮዙ ሥራዎችን በቴክኖሎጂ ጭምር በመታገዝ መሥራት እና የጸረ ሙስና ትግሉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ መቻሉን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማኅበራዊ ሚድያ የትስስር ገጽ ላይ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን