
ባሕር ዳር፡ ጥር 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ መልካሙ ፀጋዬ 85ኛውን የአገው ፈረሰኞች ክብረ በዓል በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ሙሉ መልእክቱ ቀጥሎ ቀርቧል፦
እንኳን ለ85ኛው የአገው ፈረሰኞች ክብረ በዓል በሰላም አደረሳችሁ! ክልላችን በርካታ የሚዳሰሱ ቅርሶችና የማይዳሰሱ ባህላዊ ሃብቶች ባለቤት ነው፡፡ ከማይዳሰሱት ባሕላዊ ሃብቶቻችን መካከልም የአገው ፈረሰኞች ማኅበር እና በየዓመቱ የሚከበረው የማኅበሩ ክብረ-በዓል አንዱ ነው፡፡
የአገው የፈረሰኞች ማኅበር ረጅም ታሪክ ያለው፤ የአገው ሕዝብ መገለጫ እየሆነ የመጣ ባሕላዊ ሃብት ነው፡፡
የማኅበሩ አመሰራረትና የበዓሉ አከባበር ከ1928-1933 ዓ.ም ከተካሄደዉ የጣሊያን ወረራ ጋር የተያያዘ ታሪክ እንዳለው ከታሪክ ድርሳናትና ከአባቶች ያገኘነዉ መረጃ እንረዳለን፡፡ የአገው አርበኞች ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በአንድነት ሆነው በዚያ ዘመን ጠላት ሀገራችንን ለመውረር፤ ዳር ድንበሯን ለመድፈር በተነሳበት ጊዜ በፈረሶቻቸው ዘምተው የጠላትን አንገት አስደፍተዋል፡፡ በዚህም የአገው ጀግኖች የፈረሶቻቸውን የጦር አርበኝነት ለመዘከር ማኅበር አቋቁመው ለአሁኑ ትውልድ አስተላልፈዋል፡፡
የአገው ፈረሰኞች ማኅበርም ከዚያ ዘመን ጀምሮ በተለያየ መልኩ አደረጃጀቱን እያጠናከረ፣ አባላቱን እያሰፋ እና በየዓመቱ ክብረ በዓሉን እያከበረ የዘለቀ የዘላቂ ተቋም ግንባታ ተምሳሌት የሆነ ትልቅ ተቋም ነው፡፡
በተለይም ላለፉት 84 ዓመታት ሲከበር የኖረዉና ዘንድሮም ለ85ኛ ጊዜ በመከበር ላይ ያለዉ የአገዉ የፈረሰኞች ክብረ-በዓል፤ የአገው ሕዝብን ዕምነትና ጀግንነት አጣምሮ ከዘመን ዘመን እየተሸጋገረ አሁን ላይ የደረሰ ትልቅ ሁነት ነዉ፡፡
የአገው ፈረሰኞች ክብረ በዓልን ስናከብር ሁሌም የአባቶቻችንን አርበኝነት፣ የአልደፈርም ባይነትን፣ ለብሔራዊ ሉዓላዊነት መቆምን፣ እውነተኛ ተጋድሎን እንዲሁም ለኢትዮጵያ አንድነት ያላቸውን ጽኑ እምነትና ቁርጠኝነት በውል ያስታውሰናል፡፡
የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ታሪክን ከአሁናዊ ክዋኔ ጋር አዋህዶ፣ ባሕላዊ እሴትንና ማኅበራዊ ወግን ጠብቆ ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ ቅርሳችን ነው፡፡ የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ለክልላችን እሴት ብቻ ሳይሆን ድምቀትም ውበትም ነው፡፡ ሁላችንም ልንጠብቀው፣ ልናለማውና ልናጎለብተው ይገባል፡፡
የአብክመ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮም ልክ እንደሌሎች ባሕላዊ ክብረ በዓላትና ቅርሶች ሁሉ ለአገው ፈረሰኞች በዓልም ባሕላዊ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበርና እንዲለማ ኃላፊነቱን ይወጣል፡፡
በድጋሚ እንኳን አደረሳችሁ!!
መልካም በዓል እንዲሆንልን እመኛለሁ!!
መልካሙ ፀጋዬ ገላው
የአብክመ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!