
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 25/2012 ዓ.ም (አብመድ) ዛሬ በሁለት ኢትዮጵውያን ላይ የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው ጤና ሚኒስቴር ማሳወቁ ይታወሳል፡፡
ሁለቱም የውጭ ሀገር ጉዞ ታሪክ የሌላቸውና በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪ ስለመኖራቸውም ያልታወቁ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችም 135 ደርሰዋል፤ አሐዙም በየቀኑ እየጨመረ ነው፡፡ እንደ ጤና ሚኒስቴር ገለጻ አንደኛው ግለሰብ በአዲስ አበባ በጤና ተቋም ተኝተው በመታከም ላይ እያሉ ከተወሰደ ናሙና ነው ቫይረሱ የተገኘባቸው፤ መኖሪያቸውም ዝዋይ ነው፡፡ ሁለተኛዋ ደግሞ በቤት ለቤት ቅኝት ወቅት በተወሰደ ናሙና ነው የኮሮና ቫይረስ እንዳለባቸው የተረጋገጠው፡፡ መኖሪያቸውም ደቡብ ክልል ስልጤ ወረዳ ነው፡፡
አሁን ላይ እየተደረገ ያለው ጥንቃቄም የኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ እንደገባ ይደረግ ከነበረው ያነሰ፣ ከፍተኛ መዘናጋት የሚስተዋልበት እንደሆነ አብመድ እየዘገበ ይገኛል፡፡ የጤና ባለሙያዎች፣ የጤና ዘርፍ ምሁራን እና መንግሥትም ቸልተኝነቱ አስከፊ እልቂት እንዳያስከትል ሁሉም ሰው ኃላፊነቱን እንዲወጣ እየመከሩም፣ እያሳሰቡም ይገኛሉ፡፡
አሁን ላይ በገበያ ቦታዎች፣ በታክሲ እና የባንክ ወረፋዎች፣ በየመጠጥ ግሮሰሪዎች ሰዎች ከወትሮው ባልተለዬ መልኩ ተሰባስበው እንመለከታለን፡፡ እንደ ጫት ቤቶች ባሉ የተከለከሉ አካባቢዎች ተሰባስበው በተገኙት ላይ ፖሊስ ርምጃ እየወሰደ እንደሆነም እየተገለጸ ነው፡፡ በሕዝብ መጓጓዣ ተሽከርካሪዎች ላይ የተሳፋሪዎችን ቁጥር በግማሽ ቀንሶ መጫን ላይ፣ ከፍተኛ ንክኪ በሚፈጠርባቸው ባጃጆች እና ሞተር ሳይክሎች ላይም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመተግበር ላይ በተለይም የወረዳ እና የገጠር ከተሞች ላይ የተዘነጋ ይመስላል፡፡
“ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ!” የሚለውን መልካምና ሕይወት አድን ምክር ችላ ማለቱ ደግሞ ነገ አስከፊ ዋጋ እንዳያስከፍል የሚያሰጋ፣ ሊታሰብበትም የሚገባ ነው፡፡ በዓለም ላይ እስካሁን ከ3 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ለሕመም እና ከ244 ሺህ 975 በላይ ሰዎችን ለሞት የዳረገውን ወረርሽኝ በቸልተኝነት መመልከቱም ሌላ እንቆቅልሽ ሆኗል፡፡
በአማራ ክልል አስካሁን በ6 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል፤ ሦስቱ ደግሞ አገግመዋል፡፡ የኮሮና ቫይረስ ከውጭ ሀገራት ከመጡት እና በቫይረሱ ከተያዙት ጋር ንክኪ ካለቸው ሰዎች ባለፈ በዚህ መልኩ መገኘት መጀመሩ አሁን እየታዬ ካለው መዘናጋት አንጻር ሲታይ ሁሉም ኃላፊነቱን ካልተወጣ ሊከሰት የሚችለውን አስከፊ ውጤት መገመት አያዳግትም፡፡
እርስዎስ በወረርሽኙ ላለመያዝና ወደ ሌሎችም ላለማዛመት ምን ጥንቃቄ እያደረጉ ነው?