
አዲስ አበባ: ጥር 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አሚኮ መልካም ሥነምግባር የተላበሱ ጋዜጠኞች እና የሚዲያ መሪዎች ያሉት ተቋም መኾኑ በኢትዮጵያ የሚዲያ ታሪክ ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ የአሚኮ አዲስ አበባ ስቱዲዮን የጎበኙ የፌዴራል ተቋማት የሥራ ኀላፊዎች ተናግረዋል።
ሚዲያው ሙያዊ ሥነምግባርን አክብረው የሚሠሩ ባለሙያዎች ያሉት መኾኑ ደግሞ ውጤታማ ሥራን እንዲሠራ አስችሎታል ብለዋል። አሚኮ በአዲስ አበባ ያስገነባውን አዲስ ዘመናዊ ስቱዲዮ የጎበኙት የፌዴራል ተቋማት የሥራ ኀላፊዎች አሚኮ በብዙ ውጣውረዶች ተፈትኖ ያለፈ በየጊዜውም ራሱን በማዘመን ተወዳዳሪ እና ተደራሽነቱን እያሰፋ የሚገኝ ታላቅ ሚዲያ መኾኑንም አብራርተዋል።
በተለይ አሚኮ ባለፉት 30 ዓመታት በመጣበት ጉዞ ሙያዊ ሥነምግባርን አክብረው በሚሠሩ ጋዜጠኞቹ እና የሥራ ኀላፊዎቹ የአማራን ሕዝብም ኾነ የመላው ኢትዮጵያውያንን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ነው ብለዋል።
ሀገራዊ አንድነት እና አብሮነትን በማጠንከር ረገድ የሠራው ሥራ ታላቅ ምሥጋና እና ክብር የሚሰጠው መኾኑንም አንስተዋል። ላለፉት 30 ዓመታት የሕዝቦች አብሮነት፣ ልማት እና ዕድገት ላይ የሠራው አሚኮ ራሱን በቴክኖሎጂ እና በብቁ የሰው ኅይል በመገንባት ተደራሽነቱን እያሳደገ መጥቷል ነው ያሉት።
እንደሀገር ለግጭት መንስኤ የኾኑ ችግሮችን በማስቀረት የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር እና አብሮነትን በማጠናከር አሚኮ እየሠራ ያለውን ሥራ ማጠናከር እንደሚገባው የፌዴራል ተቋማት የሥራ ኀላፊዎች አመላክተዋል።
አሚኮ ለሕዝቦች አብሮነት ለሀገር ልማት እና ዕድገት እየሠራ የሚገኝ ግዙፍ የሚዲያ ተቋም መኾኑንም አንስተዋል። መረጃዎችን ለማኅበረሰቡ በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ በአዲስ አበባ ያስገነባው አዲስ ዘመናዊ ስቱዲዮ ከሀገር ውስጥ አልፎ ዓለም አቀፍ ተደራሽነቱን እና ተወዳዳሪነቱን ከፍ ለማድረግ ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።
አሚኮ አሁን የጀመራቸውን ሥራዎች አጠናክሮ በማስቀጠል የሕዝቦችን አንድነት በማጎልበት ሀገር ከገባችበት ችግር የምትወጣበትን አማራጭ የመፍትሔ ሃሳብ ማመለካት አለበት ነው ያሉት። አብሮነትን የሚያጠናክሩ የጋራ እሴቶች እንዲዳብሩ፣ ፈጣን እና ተአማኒ መረጃን ለሕዝቡ ማድረስ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራቱን መቀጠል እንደሚገባውም አሳስበዋል። ለዚህ ሥራ ስኬትም በጋራ እንሠራለን ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ሰለሞን አሰፌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!