“እየተከናወኑ ያሉ መሠረተ ልማቶች የነዋሪዎችን ፍላጎት የሚመጥኑ ናቸው” ኢንጅነር አይሻ መሐመድ

32

አዲስ አበባ: ጥር 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የብልጽግና ፓርቲ ጉባኤ ተሳታፊዎች በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን እና ግንባታቸው ተጠናቅቆ አገልግሎት እየሠጡ የሚገኙ መሠረተ ልማቶችን ጎብኝተዋል።

የጉባኤው ተሳታፊዎች ከጎበኟቸው መካከል የነገዋ ሴቶች ተሐድሶ እና ክህሎት ማዕከል፣ የብርሃን ዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት፣ የገላን ጉራ የልማት ተነሽዎች መንደር፣ የእንስሳት ልማት ልህቀት ማዕከል ተጠቃሽ ናቸው።

በጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ የንጹህ መጠጥ ውኃ፣ የጤና፣ የትምህርት፣ የመዝናኛ እና የገቢያ ማዕከላት በጥራት እና በፍጥነት በመገንባት የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ መቻሉ የሚደነቅ መኾኑን ጎብኝዎች አንስተዋል።

በቀጣይ የአዲስ አበባን የልማት ተሞክሮ በመውሰድ አካባቢያቸውን ለማልማት እና የኅብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንደሚሠሩም ጎብኝዎቹ ተናግረዋል።

በጉብኝቱ የተገኙት የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሐመድ በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች የነዋሪዎችን ፍላጎት የሚመጥኑ ናቸው ብለዋል።

በተለይም በከተማ ግብርና፣ በአረንጓዴ ልማት፣ በቤቶች ልማት እና በኮሪደር ልማት እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ሠው ተኮር መኾናቸውንም በጉብኝታችን ያረጋገጥንበት ነው ብለዋል ።

በከተማዋ ያለውን የልማት ተሞክሮ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በማስፋት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባም ሚኒስትሯ አሳስበዋል።

ዘጋቢ:- ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየደቡብ ሱዳን ሕዝቦች ነጻነት ንቅናቄ ዋና ጸሐፊ ፒተር ላም ቦዝ በብልጽግና ፓርቲ ጉባዔ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ገቡ።
Next article“ሚስ አገው” ዛሬ ከቆይታ በኃላ ትታወቃለች።