“ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ እንዳይመጡ በማድረግ የሚገኝ ድልም ሆነ ዕድል የለም”የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ

30

ጎንደር: ጥር 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የስድስት ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ በጎንደር ከተማ አካሂዷል። የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ኢየሩስ መንግሥቱ” ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ እንዳይመጡ በማድረግ የሚገኝ ድልም ሆነ ዕድል የለም” ብለዋል።

በክልሉ በ2017 የትምህርት ዘመን 7 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመዝገብ መታቀዱን ያስታወሱት ምክትል ኀላፊዋ በክልሉ የሰላም መደፍረስ ምክንያት 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ተማሪዎች ብቻ መመዝገባቸውን ገልጸዋል። ከተመዘገቡ ተማሪዎች መካከል 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ተማሪዎች ብቻ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ ነው ያሉት። በክልሉ በሰላም እጦት ምክንያት ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን እና በመምህራን ላይ አካላዊ ጉዳት እየደረሰ እንደሚገኝ አንስተዋል።

በሰላም እጦት ምክንያት ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መኾናቸው እና 3 ሺህ 733 ትምህርት ቤቶች ትምህርት አለመጀመራቸውን ተናግረዋል። በክልሉ ለሁለት ዙር የተማሪዎች ምዝገባ መካሄዱን ያነሱት ምክትል ኀላፊዋ ያልተመዘገቡ ተማሪዎችን ለመመዝገብ በቀጣይም እስከ የካቲት 30 3ኛ ዙር ምዝገባ ይቀጥላል ብለዋል።

ዘግይተው ወደ ትምህርት ተቋማት ለገቡ ተማሪዎች የማካካሻ ትምህርት እንደሚሰጥ ገልጸዋል። በቀጣይ ትምህርት ያልጀመሩ አካባቢዎችን ለማስጀመር በትኩረት ይሠራል ነው ያሉት። የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ክንዱ ዘውዱ በዞኑ 600 ትምህርት ቤቶች ማስተማር አለመጀመራቸውን አንስተዋል። በቀጣይ ለማስጀመርም ከኅብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እንደሚሠራም ተናግረዋል።

የሰሜን ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ክቡር አሰፋ ከ100 በላይ ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን ገልጸዋል። ከማኅበረሰቡ ጋር በመናበብ በተሠሩ ሥራዎች በቅርብ ጊዜያት ውስጥ 35 ትምህርት ቤቶች እንዲጀመሩ መደረጉን ገልጸዋል።

በክልሉ ከ2 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ባለው የሰላም እጦት ምክንያት ጉዳት እንደደረሰባቸው በውይይቱ ተመላክቷል። የውይይቱ ተሳታፊዎች ሰላምን በማጽናት ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ማምጣት እንደሚገባ አንስተዋል።

ዘጋቢ: ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የኢትዮጵያ መንግሥት እና መሪው ብልጽግና ፓርቲ ለቀጣናው ሰላምና ብልጽግና ከሩዋንዳ ጋር ያላቸውን ትብብር አጠናክረው ይቀጥላሉ” አቶ አደም ፋራህ
Next article“የአገው ፈረሰኞች በዓል ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኝ ከሚመለከታቸው ጋር ሁሉ የጀመርነውን ሥራ አጠናክረን እንቀጥላለን”