
የዞኑ ግብርና መምሪያ ደግሞ የዕቅዱን 25 ከመቶ የሚጠጋ የአፈር ማዳበሪያ ብቻ ማሠራጨቱን አስታውቋል፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 25/2012 ዓ.ም (አብመድ) የሰሜን ጎንደር ዞን ጠለምት ወረዳ አርሶ አደሮች ወቅቱ የ2012/2013ዓ.ም የመኸር ዘር የሚዘራበት ቢሆንም የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር አየቀረበላቸው እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ የጠለምት ወረዳ አብዛኛው ክፍል የመሬት አቀማመጥ ወጣገባነት ያለውና የመንገድ ችግር ያለበት በመሆኑ የግብዓት አቅርቦቱን ለማግኘት ከስድስት ሰዓታ በላይ በእግር እንደሚጓዙ አርሶ አደሮች ለአብመድ ገልጸዋል፡፡
በተለይ የአፈር ማዳበሪ በወቅቱ የማይቀርብ ከሆነ መሬታቸው ጦም እንዳያድር ሰግተዋል፡፡ ‘‘የምርጥ ዘር አቅረቦት ቢኖር መልካም ነው፤ ካልተቻለ ግን እያቀያየርንም ለመጠቀም እንገደዳለን፤ የአፈር ማዳበሪያው ግን የግድ መቅረብ አለበት’’ ብለዋል፡፡
የጠለምት ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ኃላፊ ዮሐንስ ሞላም የግብዓት አቅርቦት እጥረት መኖሩን በመግለጽ አርሶ አደሮች ከአንድ ቀን በላይ ጉዞ በማደርግ ለእንግልት እየተዳረጉ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ በወረዳዉ ባለፈዉ የመኸር ወቅት ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ዘንቦ ስለነበር አርሶ አደሮች የዘር አህል እንዳይቸገሩ ስጋት እንዳላቸውም ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ ‘‘ምርጥ ዘር አቅርቦት በተቻለ መጠን ቢቀርብ መልከም ነው፤ ካልተቻለ ግን ከወረዳው ንጹሕ ዘር በመፈለግ ለማከፋፈል በዝግጅት ላይ ነን’’ ሲሉም አቶ ዮሐንስ ገልጸዋል፡፡
በዞኑ አዲ ዓርቃይ ወረዳ መኒወንበርጌ ቀበሌ ያገኘናቸው አርሶ አደሮች ደግሞ የአፈር ማዳበሪ በበቂ ሁኔታ እየቀረበላቸው እንደሆነና ከምርጥ ዘር አቅርቦት ጋር በተያያዘ ግን ችግር እንዳለ ገልጸዋል፡፡
በአዲ ዓርቃይ ወረዳ የአፈር ማዳበሪያ እየቀረበ ቢሆንም የዩሪያ ማዳበሪያ እጥርት መኖሩን የገለጹት ደግሞ የወረዳዉ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ አባተ ናው፡፡ ወደ ወረዳው የደረሰውን የአፈር ማዳበሪያ ዝናብ ሳይጀምር በሁሉም ቀበሌዎች እያደረሱ እንደሆነና የዩሪያ ማዳበሪያ በወቅቱ እንዲደርስ ከዞኑ ጋር እየተነጋሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡ እንደ አቶ ደሳለኝ ገለጻ አርሶ አደሩ ምርጥ ዘር የመጠቀም ፍላጎቱ እየጨመረ ቢመጣም በተፈለገዉ መንገድ አለመቅረቡን ገልጸዋል፡፡
የሰሜን ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ በተያዘው ዓመት በዞኑ 2012/2013ዓ.ም የምርት ዘመን ከ123 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በዘር ለመሸፈንና ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሠራ መሆኑን አመልክቷል፡፡ አብዛኛው የዞኑ አካባቢ የመሬት ክፍል የቢራ ገብስ አምራች ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የቢራ ገብስ ምርትን ለማሳደግ እየተሠራ እንደሆነም የመምሪያ ኃላፊ አራጋው ገብርማርያም ለአብመድ ገልጸዋል፡፡
በዞኑ በምርት ዘመኑ ከ73 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ እንደሚያስፈልግ ቢታወቅም በወቅቱ እየቀረበ አለመሆኑንም አቶ አራጋው ገልጸዋል፡፡ በዞኑ ለ2012/2013ዓ.ም የምርት ዘመን ከሚያስፈልገው 73 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ የተሰራጨው 18 ሺህ ኩንታል ብቻ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡ ክረምት እየቀረበ በመሆኑና የሰሜን ጎንደር ዞን አብዛኞቹ ወረዳዎች በቂ መንገድ የሌላቸው በመሆኑ ግብዓቶች በወቅቱ እንዲቀርቡ ከክልሉ መንግሥት ጋር በመነጋገር በልዩነት እንዲሠራ እየጠየቁ መሆናቸውንም የመምሪ ኃላፊ ገልጸዋል፡፡
የምርጥ ዘር አቅርቦትም ቢሆን እንደ ክልል እጥረት መኖሩን ያነሱት ኃላፊው ዞኑ አብዛኛው ክፍል ገብስ አብቃይ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የቢራ ገብስ ምርት ዘርም እየቀረበላቸዉ እንዳልሆነና ችግሩን ለመቅረፍ ከወረዳ ወረዳ በማቀያየር ለመዝራት ከ112 ኩንታል በላይ የቢራ ገብስ ግዥ መፈጸማቸውን አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደስታ ካሳ