
ባሕር ዳር: ጥር 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ ከየካቲት 1 አስከ 2 / 2017 ዓ.ም ለሁለት ቀናት በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት ያደርጋሉ ተብሏል።
በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ጉብኝት ከከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። ማኔጂንግ ዳይሬክተሯ እ.ኤ.አ በ2019 የተቋሙ ኀላፊ ከሆኑ በኋላ በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት ሲያደርጉ ይህ የመጀመሪያቸው እንደኾነ ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
በጉብኝታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እና ከከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች ጋር በኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት፣ ቅድሚያ በሚሳጣቸው ፖሊሲዎች እና በኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ዙሪያ ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
ከግሉ ዘርፍ ተወካዮች ጋር በኢትዮጵያ ስላለው የንግድ ሁኔታ እና በኢኮኖሚ እድሎች ዙሪያ ውይይት ያደርጋሉ ነው የተባለው። በሀገሪቱ በማኅበራዊ ልማት የተሠሩ ሥራዎችን እንደሚጎበኙም ተመላክቷል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!