
ባሕር ዳር: ጥር 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሰሜን ጎጃም ዞን የ2017 የበጋ የተፈጥሮ ሀብት ልማት እና ጥበቃ የማስጀመሪያ ንቅናቄ በይልማና ዴንሳ ወረዳ መሰቦ ቀበሌ ጭንጫ ተፋሰስ ላይ አስጀምሯል። በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ የቀበሌው አርሶ አደሮች፣ የወረዳ እና የዞን መሪዎች እንዲኺም የመከላከያ መሪዎች ተገኝተዋል።
የሰሜን ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ መልካሙ አለኸኝ ለዘንድሮው የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ በቂ የቅድመ ዝግጅት ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል። በዞኑ 14 ሺህ 994 ሄክታር ማሳ ላይ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ እንደሚሠራ ገልጸው ዛሬ በይልማና ዴንሳ ወረዳ መሰቦ ቀበሌ ጭንጫ ተፋሰስ ላይ እያስጀመርን ነው ብለዋል።
የይልማና ዴንሳ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጌትነት አሰፋ የቅድመ ዝግጅት ሥራ መሠራቱን እና ከሕዝቡ ጋር ውይይት በማድረግ እና በመግባባት ልማቱ መጀመሩን ተናግረዋል። የይልማና ዴንሳ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ይበልጣል ሙላቴ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራው ላይ ችግር ፈጥሮ መቆየቱን ገልጸው ዘንድሮ ያንን ጨምሮ የሚክስ ሥራ እንደሚሠራ ጠቁመዋል።
በሰላም እጦቱ የግብርና ባለሙያዎችም ለመሥራት ተቸግረው በመቆየታቸው ሕዝብን ለማገልገል አስቸግሮ እንደነበር ጠቅሰዋል። ሕዝቡ ልማቱ አፈራችን ከጎርፍ ለማስቀረት በመኾኑ እንሠራለን እናንተ ሙያዊ ድጋፍ አድርጉልን ማለቱን የጠቀሱት የወረዳ አሥተዳዳሪው የግብርና ልማቱ እንዲቀጥል መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።
የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ የሕይዎት መሠረት መኾኑ ስለሚታወቅ የሞት ሽረት ጉዳይ አድርገን እንሠራለን፤ በዚህም 1 ሺህ 95 ሄክታር ማሳ ይለማል፤ ከዚህ በፊት የተሠሩትንም በማጠናከር እያለማን ነው ብለዋል አሥተዳዳሪው። የወል መሬቶችን በማኅበር በማደራጀት ለኅብረተሰቡ በማስረከብ፣ ልቅ ግጦሽን በማስቀረት እና ሳሩን አጭዶ እንዲጠቀም በማድረግ እያለሙ ስለመኾኑም ነው የጠቆሙት።
የሰሜን ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ በለጠ ጥጋቤ ባለፈው ዓመት የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ መሥራት አለመቻሉን አስታውሰው የመከላከያ ሠራዊት መስዋዕትነት ከፍሎ ባስከበረው ሰላም ዘንድሮ ልማት መሥራት መቻላቸውን ነው ያስገነዘቡት። የሰላምን ዋጋ አይለካም ያሉት ኀላፊው የይልማና ዴንሳ ወረዳ ሕዝብ ሰላሙን ለማዝለቅ እና ልማቱን ለማስቀጠል ከልቡ ለሰላም መቆም አለበት ብለዋል።
ይልማና ዴንሳ ወረዳ የሚታወቀው በምርቱ ነው ይህንን ሠርቶ አደርነት ሊያስቀጥል ከኾነ ለሰላም መቆም አለበት ነው ያሉት። ምርት እና ምርታማነት እንዲያድግ የተፈጥሮ ሀብት ልማት መሥራት ያስፈልጋል፤ የማዳበሪያ ፍላጎትም የሚጨምረው የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ በበቂ እና በአግባቡ ስላልተሠራ ነው፤ ስለዚህ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራን በትኩረት መሥራት እና ማስቀጠል ያስፈልጋል ብለዋል።
በመከላከያ ሠራዊት የምሥራቅ ዕዝ የኮር አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል አዲሱ ሙሐመድ ”ጽንፈኛው ኀይል የመከላከያ ሠራዊትን ስም በማጥፋት ከሕዝቡ ሊለያየን ሞክሯል፤ ነገር ግን በከፈልነው መስዋዕትነት ሰላም አስፍነናል” ብለዋል። እኛ የእናንተ ልጆች ጠባቂዎች ነን ነው ያሉት። በአማራ ክልል መንግሥት ጥያቄ መሠረት ሕገ መንግሥትን ለማስከበር ወደ አካባቢው መግባታቸውንም አስገንዝበዋል።
መከላከያ ሠራዊት የሚንቀሳቀሰው ሰላምን በማስከበር ልማትን ለማስቀጠል መኾኑንም ገልጸዋል። ለአማራ ቆምኩ የሚለው አካል መሠረተ ልማቶችን በማስቆም፣ ትምህርት በመዝጋት፣ ጉዞ በመከልከል ሕዝብን እያሰቃየ ነው ያሉት ብርጋዴር ጄኔራል አዲሱ ሕዝቡ ግፍ እየደረሰበት መኾኑንም ተናግረዋል።
ጦርነት ሰላምን አጥፍቶ ልማትን አስቁሞ አቅም የሌላት ሀገር ይፈጥራል እና ሕዝቡ ችግሩን ተገንዝቦ ግጭት እና ጦርነት በቃኝ ሊል ይገባል ብለዋል።
የሃይማኖት አባቶች እና እናቶች እየተገደሉ ባለበት ሁኔታ ለአማራ ተቆረቆርኩ ማለት አይቻልም ነው ያሉት። በግጭቱ የአማራ ሕዝብ ትውልዱን እያጣ ነው። ሥልጣን የሚያዘው በሕዝብ ምርጫ ብቻ እንጂ በአፈ ሙዝ ስላልኾነ ሕዝቡ ጦርነት ቀስቃሾችን ተው ሊል ይገባል ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!