
ባሕር ዳር: ጥር 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር የጸጥታ ተቋማት የበጀት ዓመቱን የስድስት ወራት የሕግ ማስከበር ተግባራት አፈጻጸም ግምገማ እየተካሄደ ነው።
አሁን ያለው አንጻራዊ ሰላም እንድመጣ የጸጥታ መዋቅሩ ላደረገው ትግል እና መስዋዕትነት ምስጋና ይገበዋል ያሉት የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ስለሽ ተመስገን ናቸው።
ሰላም የአንድ ወገን ብቻ ሳይኾን የሁሉንም ማኅበረሰብ ተሳትፎ ስለሚጠይቅ ማኅበረሰቡን ያሳተፈ የሰላም ማስከበር ተግባራትን አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በከተማችን የዝርፊያ እና የአፈና ወንጀሎች እየተበራከቱ በመኾኑ ይህን ሊቀለብስ የሚችል የጸጥታ ኀይል መገንባት ያስፈልጋልም ብለዋል።
የውይይቱ ዓላማ በከተማው ሕግ በማስከበር ሥራዎች የነበሩ ጥንካሬዎችን በማስቀጠል እና የነበሩ ድክመቶችን ደግሞ በማረም ወደ ተግባር ለመግባት ነው ያሉት ደግሞ የከተማ አሥተዳደሩ ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ይሄነው አበባው ናቸው።
በግምገማው የከተማ አሥተዳደሩ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ የመምሪያ እና የክፍለ ከተማ አሥተዳደር የጸጥታ፣ የሚሊሻ፣ የፖሊስ እና የአድማ መከላከል የሥራ ኀላፊዎች እና አሥተባባሪዎች እየተሳተፍ መኾኑን ከደብረ ማርቆስ ከተማ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!