
ባሕር ዳር: ጥር 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ አስተባባሪነት የተዘጋጀው የባሕል አውደርዕይ መካሄድ ጀምሯል።
የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ጋሻው እንዳለው በ”ጥርን በባሕርዳር” እንደ ከተማ እየተካሄደ ባለው ልዩ ዝግጅት ባሕላዊና ሃይማኖታዊ በዓላትን መከበራቸውን ገልጸዋል። በበዓላቱ ከፍተኛ ስኬት የታየበት ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት።
የባሕል አውደርዕዩ በከተማዋ እና አካባቢዋ የሚገኙ የባሕል ውጤቶችን ለማስተዋወቅ ፣አምራች እና ሸማቾችን በማገናኘት፣ የገበያና ግብይት እንቅስቃሴውን ለማሳደግ ጥሩ አጋጣሚ መኾኑን ገልጸዋል። እምቅ የባሕል ሀብቶችን በመጠበቅ ለጋራ ተጠቃሚነት ማዋል ይገባልም ብለዋል።
የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ጊዜው ታከለ ባሕርዳር በጥር ወር በልዩ ልዩ ዝግጅቶች የደመቀችበት ፣የቱሪዝም መነቃቃት እንዲፈጠር ጥረት የተደረገበት፣ የከተማዋ ማኅበራዊ ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስተጋብሮች ወደ ተሻለ እንቅስቃሴ የተሸጋገሩበት ወቅት ነው ብለዋል።
መሰል የለውጥ ተግባራትን ለበለጠ ስኬታማነት አቀናጅቶ መምራት እንደሚገባ ተናግረዋል። ባሕርዳር የሰላም ፣የለውጥ እና የአንድንት ከተማ ኾና እንድትቀጥል ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል። ጥርን በባሕርዳር የሚታደሙ ገብኝዎችን ደኅንነት መጠበቅ እና ከተማዋን ለቱሪዝም የተመቸች ማድረግ ከሁሉም ይጠበቃል ነው ያሉት።
የከተማዋን ሰላም እና ልማት እንዲቀጥል የሁሉንም አካል የጋራ ጥረት የሚጠይቅ መኾኑንም ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!