
ባሕር ዳር: ጥር 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ዲፕሲክ” የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሥርዓት የተላበሰ ቻትቦት ነው፡፡ ቻትቦት ማለት የሰው ሠራሽ አስተውሎት እንዲኖረው ከተደረገ ኮምፒውተር አልያም ‘ስማርት’ ስልክ ጋር በጹሑፍ በሚከናወን ተግባቦት የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት የሚያግዝ መተግበሪያ ነው፡፡
ቻትቦቶች እንደሚሰጡት አገልግሎት በአንድ ጉዳይ ላይ ብቻ መረጃ የሚሰጡ እና ሁለገብ አቅም ያላቸው በሚል ሰፊ ክፍል ሊመደቡ ይችላሉ፡፡ እንደሌሎች ቻትቦቶች ዲንሲክ በጹሑፍ በምንሰጠው መመሪያ ወይም ፕሮምት ለምናቀርብለት ጥያቄ መልስ የሚሰጥ የሰው ሠራሽ አስተውሎትን የተላበሰ የተግባቦት አማራጭ ነው።
ከአሠራር እና አገልግሎት አንፃር ከቻትጂፒቲ ጋር የሚቀራረብ ነው። ሁለቱም ቻትቦቶች ተመሳሳይ ሥራዎች ለመሥራት ጥቅም ላይ ቢውሉም የትኛው የተሻለ ነው የሚለው አከራካሪ ኾኗል። እንደ አብዛኞቹ የቻይና ቴክኖሎጂዎች “ዲፕሲክ” ያልተገቡ የፖለቲካ ይዘቶችን አይቀበልም። እንዲህ አይነት ጥያቄ በሚቀርብለት ጊዜ “ይቅርታ! ይህን ጥያቄ መመለስ አልችልም፤ እኔ ጠቃሚ እና ጉዳት የሌላቸውን ምላሾች ለመስጠት የተፈጠርኩ አጋዥ ነኝ” የሚል መልስ ይሰጣል።
የዚህ ዝነኛ መተግበሪያ ባለቤት ሊያንግ ዌንፌንግ የተባለ በብዙዎች ዘንድ የማይታወቅ የኤሌክትሮኒክስ ኢንፎርሜሽን ምህንድስና እና ኮምፒውተር ሳይንስ ምሁር ነው ። ይህ ሰው በቅርቡ የቻይና ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኪያንግ ባዘጋጁት ጉባኤ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘርፍ ዲፕሲክ ያገኘውን ዕውቅና አስመልክቶ ለመናገር ብቅ ብሎ የነበረ ሰው ነው፡፡
በመተግበሪያ ቋንቋ ለመቀመር እና የሒሳብ ስሌቶችን በማስላት “ዲፕሲክ” የላቀ ሲኾን ብዙ ቅደም ተከተል ያላቸውን መልመጃዎች በመሥራት እና ከጹሑፍ ተጨማሪ ምስልን በመጠቀም “ቻትጂፒቲ” የተሻለ መኾኑ ታውቋል። ከአፕስቶር መተግበሪያ ቋቶች በብዛት ወርዶ በመጫን ቁንጮ ላይ መቀመጥ የቻለ እና የብዙዎችን ቀልብ መያዝ የቻለ “ቻትቦት” ነው።
በቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ትኩረት ከመፍጠሩ እና ለዓለም ከመድረሱ በፊት ቀድመው ማየት የቻሉ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ባለሙያዎች ተደምመውበት እንደነበረም የቢቢሲ ዘገባ አመላክቷል። ተጽዕኖው ትልቅ በመኾኑ አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ትራም ሳይቀር ይህን ቴክኖሎጂ አስመልክተው ለሀገራቸው የቴክ ኩባንያዎች መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ኩባንያዎቹ አሜሪካን በዘርፉ ከፍ ለማድረግ ይችሉ ዘንድ ቻይና ሠራሹ የሰው ሠራሽ አስተውሎት የተላበሰ ቻትቦት ‘የማንቂያ ደወል’ ነው ማለታቸውን ቢቢሲ አክሏል። ቴክኖሎጂው እንደ “ጄሚናይ” እና “ቻትጂፒቲ” ካሉ መተግበሪያዎች በጣም ልዩ ያደርገዋል ያስባለው በጣም ዝቅተኛ በሚባል ወጭ በመልማቱ ነው፡፡
ይህ ሊኾን የቻለው ደግሞ በቁጥር ውስን የኾኑ የዝማኔ ደረጃቸው ግን የላቀ የኤሌክትሮኒክስ ቺፖችን በመጠቀሙ ነው። የቴክኖሎጂ የበላይነት ፉክክሩ ብርቱ በኾነበት በዚህ ወቅት የበላይነቱን ለመንጠቅ በመተግበሪያው ላይ በርካታ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች እየተሰነዘሩበት መኾኑንም ዘገባው ጠቁሟል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!