
ባሕር ዳር: ጥር 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ከሞሮኮው ናሽናል ራሊ ኦፍ ኢንዲፔንደንትስ(አር ኤን አይ) ፓርቲ ተወካይ ፕሮፌሰር መሐመድ ሳዲኪ ጋር ተወያይተዋል።
የሞሮኮ ናሽናል ራሊ ኦፍ ኢንዲፔንደንትስ ፓርቲ ተወካይ ፕሮፌሰር መሐመድ ሳዲኪ በብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ለመታደም ትናንት ማምሻውን አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወሳል። በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ በውይይታቸውም የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባኤ የተመዘገቡ ስኬቶችን በማጽናት ለቀጣይ ቁርጠኝነታችንን የምናድስበት ነው ብለዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ለሕዝብ የገባውን ቃል በተግባር በመፈጸም የሁሉም ኢትዮጵያውያን ድምፅ መኾኑን በተግባር ማሳየቱንም ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት እንዲመዘገብ፣ የሕዝቦች አንድነትና ትብብር እንዲጎለብት ብልጽግና ፓርቲ የሚመራው መንግሥት ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቡንም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ እና ሞሮኮ የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላቸው ሀገሮች መሆናቸውን የገለጹት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፣ በፓርቲ ደረጃ ያላቸው ትብብርም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። የሞሮኮ ናሽናል ራሊ ኦፍ ኢንዲፔንደንትስ ፓርቲ ተወካይ ፕሮፌሰር መሀመድ ሳዲኪ በበኩላቸው በብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ በመገኘቴ ደስተኛ ነኝ ብለዋል።
በመጀመሪያው ጉባኤ የተገባውን ቃል በመፈጸም ለዚህ የድል ምዕራፍ ስለደረሳችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ነው ያሉት። ኢትዮጵያና ሞሮኮ የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላቸው ሀገሮች መሆናቸውን የገለጹት ፕሮፌሰሩ በታዳሽ ኀይል፣ በግብርናና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ በጋራ እንደሚሠሩም አረጋግጠዋል።
ኢዜአ እንደዘገበው የደቡብ ለደቡብ ትብብር፣ የሁለትዮሽ ግንኙነታችንን በማጠናከር በተፈጥሮ ሀብትና ሌሎች ዘርፎችም በጋራ እንሰራለን ብለዋል። በቀጣይም የብልጽግና ፓርቲ በሞሮኮ የሥራ ጉብኝት እንዲያደርግ ግብዣ አቅርበዋል። እንደ ፓርቲ ያላቸው ትብብርም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!