የአገው ፈረሰኞች በዓል ታሪኩን እና ባሕሉን በጠበቀ መልኩ እንዲከበር ዝግጅት ተጠናቅቋል።

36

እንጅባራ: ጥር 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአገው የባሕል አንባሳደር ኾና የምታገለግለው የአገው ቆንጆ “ሚስ አገው” የቁንጅና ውድድር ዛሬ ይካሄዳል። 85ኛው የአገው ፈረሰኞች በዓል በየዓመቱ ጥር 23 በእንጅባራ ከተማ በድምቀት ይከበራል። በዓሉ ከዓመት ወደ ዓመት አዳዲስ ድምቀቶችን እየያዘ የሚከበር ነው።

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ለይኩን ሲሳይ በዚህ ዓመትም ባሕል፣ ታሪኩን እና ወጉን በጠበቀ መልኩ ሊከበር ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል። የበዓሉ ዝግጅት ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁንም አስታውቋል። ከዋናው በዓል ዋዜማ ጀምሮ የበዓሉ አካል የኾኑ በርካታ ሁነቶች እየተካሄዱ እንደኾነም ተናግረዋል።

በዋዜማው መርሐ ግብር በዓሉን የተመለከተ የፓናል ውይይት ይካሄዳል። የብሔረሰቡ የባሕል አንባሳደር ኾና የምታገለግለው የአገው ቆንጆ የምትመረጥበት “ሚስ አገው” የቁንጅና ውድድርም በዋዜማው ይካሄዳል።

ከሁሉም ወረዳዎች የተወጣጡ የባሕል ቡድን አባላትም ወደ እንጅባራ ከተማ መግባታቸውን መምሪያ ኀላፊው ገልጸዋል። ጥር 23 በድንቅ ትርዕቶች ለሚከበረው በዓልም ሙሉ ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት። ለፈረሶች ትዕይንት የሜዳ ዝግጅት ተደርጓል ያሉት ኀላፊው ፈረሰኞችም መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።

ሙሉ የበዓሉ ዝግጅት በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ባሉ አማራጭ ማሰራጫዎች በቀጥታ እንደሚተላለፍ የገለጹት ኀላፊው በአካል መገኘት ያልቻሉ ሁሉ ይህንን ድንቅ በዓል በአሚኮ በኩል እንዲከታተሉም ጥሪ አቅርበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየብልጽግና ፓርቲ የጉባኤ ተሳታፊዎች በመዲናዋ የሚገኙ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እየጎበኙ ነው።
Next article“ሁለተኛው ጠቅላላ ጉባኤ የተመዘገቡ ስኬቶችን በማጽናት ለቀጣይ ቁርጠኝነታችንን የምናድስበት ነው” አቶ አደም ፋራህ