
ባሕር ዳር: ጥር 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 85ኛውን የአገው ፈረሰኞች በዓል ምክንያት በማድረግ የፓናል ውይይት እየተደረገ ነው። እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ከአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲኾን በተለይም የአሱሪቴ ባሕላዊ ትውን ጥበብ አሁን ላይ ያለበትን ኹኔታ የሚዳስስ እና በቀጣይ የበለጠ አድጎ የማኅበረሰቡ አንዱ የቱሪዝም ሀብት እንዲኾን የሚያስችል ነው ተብሏል።
የፓናል ውይይቱን የከፈቱት የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጋርዳቸው ወርቁ (ዶ.ር) ዩኒቨርሲቲው ከመደበኛ የመማር ማስተማር ሥራው በተጨማሪ የተሰጠውን ማኅበረሰባዊ ተሳትፎም እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲው ከሚሰጣቸው ማኅበራዊ ግልጋሎቶች ውስጥ የአዊ እና አካባቢውን ባሕል እና እሴቶች በማጥናት ማሳደግ አንዱ ነው ብለዋል።
አዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የበርካታ ቱባ ባሕል፣ ወግ እና እሴቶች ባለቤት መኾኑንም ገልጸዋል ፕሬዝዳንቱ። እነዚህን የሕዝብ ሀብቶች የበለጠ ለማጎልበት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ስለመኾኑም ጠቅሰዋል። ዩኒቨርሲቲው የአዊኛ ቋንቋ ትምህርት ከፍቶ እያሠለጠነ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ተከፍቶ የአካባቢውን ባሕል፣ ጥበብ እና የተፈጥሮ ሀብት በጥናት በመለየት የሚያድግበትን አቅጣጫም እያመላከተ ነው ብለዋል። በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክትል አሥተዳዳሪ አይተነው ታዴ የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ከቆየ ታሪካዊ ዳራው ባሻገር ለአኹናዊ ወንድማማችነት እና መልካም ግንኙነት ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ብለዋል።
አያቶቻችን ቅኝ ገዥዎችን አሳፍረው ለመመለስ ሲሉ የጀግንነት ዋጋ ከፍለዋል፤ ይህንን ለማስታወስም የፈረሰኞች ማኅበሩ ተመስርቷል ነው ያሉት ምክትል አሥተዳዳሪው። ፈረስ ከአገው ሕዝብ ጋር ጥብቅ እና የተለየ ቁርኝት እንዳለው ገልጸው ይህ የፈረሰኞች በዓል በደመቀ እና በልዩ ኹኔታ እንደሚከበርም ገልጸዋል።
በዓሉን ተከትሎም በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ ልዩ በኾነ ድምቀት እና እሴት የሚከበሩ ተያያዥ ጥበባዊ እና ባሕላዊ ክዋኔዎች እንዳሉም ገልጸዋል።
በፖናል ውይይቱ ላይ የተለያዩ ወረዳዎች የባሕል ቡድን አባላት ባሕላዊ ጭፈራዎችን አሳይተዋል፤ በአካባቢው ብቻ የሚገኙ ባሕላዊ ምግቦች እና መጠጦችም ቀርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!